ቢጂአይ ኢትዮጵያ እና ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ እየተወዛገቡ ነው

ቢጂአይ ኢትዮጵያ እና ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ እየተወዛገቡ ነው

በቢጂአይ ኢትዮጵያ እና በፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ መካከል ሲካሄድ የቆየው ሜክሲኮ የሚገኘው የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ ሽያጭ ድርድር፣ ውል ለማሰር ባለመቻሉ ሂደቱ መቋረጡ ተገልጧል፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ ትላንት ባሰራጨው መግለጫ፣  የሽያጩ ውል የተቋረጠው ፤ በፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ  በኩል ግብይቱን ለማጠናቀቅና የሽያጭ ውሉን ለመፈረም ፍላጎትና ቁርጠኝነት ባለመኖሩ ነው፤ ብሏል።

ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ግን በዚህ አይስማማም፡፡ ኩባንያው ዛሬ ጠዋት ሠንጋ ተራ በሚገኘው የዋና መ/ቤቱ አዳራሽ በሰጠው መግለጫ፤ ”ቢጂአይ ኢትዮጵያ የመንግሥት ግዴታዎችን ባለመወጣቱ በውልና ማስረጃ ለመፈራረም አልተቻለም“ ብሏል፡፡

ለቢጂአይ 1ቢ. 150 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙን ያስታወሰው ፐርፐዝ ብላክ፤ ቀሪውን ክፍያ በህጉ መሰረት  በውልና ማስረጃ ስንፈራረም ለመክፈል ዝግጁ ነን ብሏል፡፡

”ከታክስ ነጻ የሆኑበት ወረቀት ከቀረበ በውልና ማስረጃ እንፈራረማለን፤ እኛ ተገቢውን ሰነድ ካሟሉ በሁለተኛው ዙር የሚጠበቅብንን 2.5 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ዝግጁ ነን፡፡“ ብሏል፤ ፐርፐዝ ብላክ በሰጠው መግለጫ፡፡

ቢጂአይ ኢትዮጵያ የታክስ ክሊራንስ አቅርቦ በውልና ማስረጃ የማይፈራረም ከሆነ ግን ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ለመውሰድ እንገደዳለን ብሏል – ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ፡፡

ቢጂአይ እና ፐርፐዝ ብላክ ሜክሲኮ የሚገኘውን የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና መ/ቤት ህንጻ ለመገበያየት የተዋዋሉት በ5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ 1 ቢሊዮን ብር የቅድምያ ክፍያ መፈጸሙ ታውቋል፡፡ ከፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ የሚጠበቀው ሁለተኛ ክፍያ 2.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ይህ ክፍያ የሚፈጸመው በውልና ማስረጃ ስንፈራረም ነው ብሏል – ፐርፐዝ ብላክ በመግለጫው፡፡

የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ ለሥራ ጉዳይ በአሜሪካ እንደሚገኙና ከነገ ወዲያ ሐሙስ እንደሚመለሱ የተጠቆመ ሲሆን፤ አርብ ጠዋት በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መግለጫ ይሰጣሉ ተብሏል፡፡

ዝግጅት ክፍሉ በሁለቱም ወገን ያለውን ዝርዝር ጉዳይ እየተከታተለ ያደርሳችኋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply