ባለስልጣኑ ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው ተማሪ መዝግበው ሲያስተምሩ የነበሩ 3 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ማግኘቱን አስታወቀ

ዕረቡ ሐምሌ 6 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው ተማሪ መዝግበው ሲያስተምሩ የነበሩ ሦስት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማግኘቱን አስታውቋል።

ባለስልጣኑ ከግንቦት 13 እስከ ሰኔ 1 ቀን 2014 ድረስ በተለያዩ የክልል ከተሞች ባካሄደው ድንገተኛ ፍተሻ ነው ተቋማቱን ማግኘቱን የገለፀው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እነዚህ ተቋማት ፈጽሞ የእውቅና ፈቃድ ሳይኖራቸው በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ተማሪ መዝግበው በማስተማር ህዝቡን ለገንዘብ፣ ለጊዜና ለሞራላዊ ኪሳራ እየዳረጉ መሆኑንም አብራርቷል።

በመሆኑም “ጅኤ ኢንደስትሪያል ኮሌጅ” በአማራ ክልል (በደብረማርቆስ ከተማ እና አካባቢው)፣ “ኦሞ ቫሊ ዩኒቨርሳል ኮሌጅ” በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል (በዳውሮ ፣ በተርጫ) እንዲሁም “ሆርን ኦፍ አፍሪካ ቢዝነስ ኮሌጅ” በኦሮሚያ ክልል (በአምቦ ከተማ እና አካባቢው) ያለምንም ፍቃድ እና እውቅና ተማሪዎችን መዝግበው ሲያስተምሩ መገኘታቸውን ገልጿል።

ባለስልጣኑ የክልሎቹ መንግስታት ህግ የማስከበር ድርሻቸውን እንዲወጡ የጠየቀ ሲሆን፤ ህገ-ወጥ ተቋማቱን የከፈቱ አካላት የፈጸሟቸው የህግ ጥሰቶች ካሉ በሚመለከታቸው የፍትሕ አካላት ተጠያቂ እንደሚደረጉም አረጋግጧል።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ከዚህ በፊት በደቡብ ክልል ‘ፊንላንድ ኮሌጅ’ በሚል እና በአማራ የክልል ‘ሀምበርቾ ኮሌጅ’ በሚል ራሳቸውን የሰየሙ ህገ-ወጥ አካላት መኖራቸውን ለክልል መንግስታቱ ማሳወቁንም አስታውሷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply