ባልደራስ ለእውነተኛ እና  ዲሞክራሲ ፓርቲ ሰልፍ መጥራቱን ገለጸ

በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚፈፀሙትን ጥቃቶች ለማውገዝና የፍትሕ ስርዓቱን ለመቃወም ለጥር 9 ቀን 2013 ዓ.ም የጠራሁት ሰላማዊ ሰልፍ ይከለከላል የሚል ዕምነት የለኝም ሲል ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አስታወቀ፡፡

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ታህሳስ 20/2013 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጎ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ወሳኔ ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡

ለሰላማዊ ሰልፉ መካሄድ አራት መሰረታዊ ጭብጦች ተዘርዝረዋል፡፡ በኢትዮጵያ  ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በተደጋጋሚ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን፣ በወለጋ፣ በጉራፈርዳና በሰገን ህዝቦች ቀጣና አካባቢ እንዲሁም በጉማይዴ ህዝብ ላይ የተካሄደውን የዘር ማጥፋትን መቃወም የሚለው ቀዳሚው ነው፡፡

በሁለተኛነት የሱዳንን የድንበር ጥሰትን መቃወም፤ ሶስተኛ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ ስለሚገነባቸው ግንባታዎች ጉዳዩ እንዲሁም  ስለፓርቲው አመራሮች እስር እና ዳተኛ ስለሆነው የፍትህ ሂደትን ይመለከታል፡፡

በዚህም ሰላማዊ ሰልፉ ለጥር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጠራ ሲሆን ሰላማዊ ሰልፉን የሚያስተባብር ግብረ – ኃይልም ተቋቁሟል ተብሏል፡፡

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ዶክተር በቃሉ አጥናፉ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እና ሀሳብን በነፃነት መግለፅ ህገ መንግስታዊ መብት ነው፤ ይከለከላል የሚል ዕምነትም የለኝም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

**********************************************************************************

ዘጋቢ፡ክብሮም ወር

ቀን 22/04/2013

Source: Link to the Post

Leave a Reply