
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን እንዳያደርግ በኦሮሚያ ፖሊስ መከልከሉን አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 3 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) በአራዳ ክ/ከተማ ጋምቤላ ሆቴል መጋቢት 3/2015 ሊያደርገው የነበረው ጠቅላላ ጉባኤ እንዳይደረግ ክልከላ የገጠመው መሆኑን አስታውቋል። ክልከላው የተደረገውም በዋናነት ከበላይ በመጣ ትዕዛዝ ነው ተብሏል። ከልካዮችም የኦሮሚያ ፖሊስ፣የደህንነትና መሰል የጸጥታ አካላት ናቸው የተባለ ሲሆን እዚህ እንዳታስተናግዷቸው በሚል ለባለንብረቱ ማስፈራሪያ የደረሰው ስለመሆኑ ባልደራስ አስታውቋል። ጠቅላላ ጉባኤው የተከለከለውም የምርጫ ቦርድ 3 ታዛቢዎች ባሉበት እና ምልአተ ጉባኤውም የተሟላ በሆነበት ወቅት ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ያለ የሆቴል አዳራሽ ስብሰባ ማድረግ አትችልም በሚል የከለከለው አካል የኦሮሚያ ፖሊስ እና የደህንነት አካላት መሆናቸው ነገሩን እጅግ በጣም አሳዛኝ እንደሚያደርገው ተገልጧል። ይህ አካሄድም የአዲስ አበባ መስተዳድር ከኦሮሚያ የጸጥታ አካላት ጋር ተባብረው አፈና እየፈጸሙ ስለመሆኑ አመላካች ነው ተብሏል። ምልአተ ጉባኤው ተሟልቶ በመገኘቱም ከፍተኛ ምስጋና ቀርቦለታል። ባልደራስ ከፍተኛ ዋጋ የተከፈለበት ፓርቲ ከመሆኑ አንጻር እንደዚህ ዓይነት ፈተናዎችን እንደሚያልፋቸው ተጠቁሟል። ክልከላው በተደረገበት ወቅትም የባልደራስ ም/ፕሬዝደንት አቶ አምሃ ዳኘው፣ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ እንዲሁም የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም በስፍራው ለተገኙ የሚዲያ ባለሙያዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። በስርዓቱ በኩል እየተደረገ ያለውን አፈናም በማውገዝ በቅርብ ጊዜ ለፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ዝርዝር ሂደቱን እንደሚያሳውቁ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለጋምቤላ ሆቴል ህጋዊ መሆኑን አውቆ እንዲተባበረው ደብዳቤ የጻፈ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በየካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን ለማድረግ የነበረው እቅድ የጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ አካላት ቀድመው በስርዓቱ አካላት በመታሰራቸው ጉባኤው ለመጋቢት 3/2015 መራዘሙ ይታወቃል።
Source: Link to the Post