
ባልደራስ በአባላቱ ላይ እስር እና ወከባ እየተፈጸመበት መሆኑ ተገለጸ፤ ይህም የአድዋ ድል በዓልን እንዳያከብር እና ጠቅላላ ጉባኤውን በስኬት እንዳያከናውን የታሰበ ነው ተብሏል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ከአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ጋር ቆይታ ያደረገችው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) የጽ/ቤት ኃላፊ እና የስራ አስፈጻሚ አባል ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እንደገለጸችው የባልደራስ አመራሮችና አባላት የአድዋ ድል በዓልን ከህዝብ ጋር ሆነው በድምቀት እንዳያከብሩ ጫና እየተደረገባቸው ነው። ፓርቲው የካቲት 26/2015 ጠቅላላ ጉባኤውን በተሳካ መልኩ እንዳያከናውን ያልተገባ ስርዓታዊ ጫና፣ እስር፣ ወከባ እና በደል በአባላት ላይ እየተፈጸመም ይገኛል ስትል አካሄዱን አውግዛለች። አባላትና ሌሎች ባለ ጉዳዮችም ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽ/ቤቱ ሲመጡ የካቲት 22/2015 ፍተሻ እንደተደረገባቸው እና መታወቂያ የተጠየቁ መሆኑ ተገልጧል። ወ/ሮ ቀለብ ስትቀጥል ፓርቲው እንደተለመደው ድርጅታዊ ስራውን ለማከናወን የሚችልበት ሁኔታ እንዳይኖር እየተደረገ ነው ብላለች። የደህንነት አካላት፣ ፖሊሶች ወከባ እየፈጠሩ እና ጽ/ቤቱን የከበቡ በመሆኑ አመራሮች፣አባላት እና ባለጉዳዮች ወደ ጽ/ቤት እንዳይገቡ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተገልጧል። ከ6 በላይ ፓትሮሎች እና በጣም ብዙ ሲቪልና የደንብ ልብስ የለበሱ የፀጥታ ኃይሎችን አሰማርቶበታል ተብሏል። እንደአብነትም የካቲት 21/2015 ከታሰሩት መካከል:_ 1) ከፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ሳሙኤል ዲሜትሪ፣(በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽን ሶስተኛ ታስሯል) ከቀኑ 6 ሰዓት ገደማ ነው የታሰረው። የባልደራስ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ እና ድምጽ ሰጭ አባል ነው። አቶ ሳሙኤል ዲሜትሪ (ኩባ) በወቅቱ ከ2 ዓመት የ8 ወር ልጃቸው ጋር በፖሊስ ታግተው ተወስደዋል በሚል ፓርቲው መግለጹ ይታወሳል። 2) ሄኖክ ኃይሉ፣ የጠቅላላ ጉባኤው ድምጽ ሰጭ አባልም ታስሯል። 3) ወንድሙ ጠጁ የተባለ የባልደራስ ፓርቲ ጥበቃ ሲሆን የካቲት 22/2015 ከረፋዱ 4 ሰዓት ገደማ በአዲስ አበባ ፖሊስ መነን አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ታስሯል። 4) አቶ ስንታየሁ ቸኮል_ከቅዱስ ሲኖዶስ ጥቁር ልበሱ ትዕዛዝ ጋር በተያያዘ ከጎፋ ገብርኤል ተይዞ ወደ አዋሽ አርባ ከተወሰደ አንድ ወር ገደማ ቢሆነውም እስካሁን ፍትህ አላገኘም። 5) በዓል በመጣ ቁጥር በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ማንነትና ልብስ መረጣ፣ ያልተገባ ወከባ፣ እስር እና ማሳደድ ሊቆም እንደሚገባውም ተመላክቷል።
Source: Link to the Post