ባልደራስ ዛሬ በፌደራሊዝም ጽንሰ ሀሳብ ላይ እነ ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና አቶ ማሙሸት አማረ በተገኙበት ውይይት አደረገ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 15 ቀን 2013 ዓ.ም…

ባልደራስ ዛሬ በፌደራሊዝም ጽንሰ ሀሳብ ላይ እነ ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና አቶ ማሙሸት አማረ በተገኙበት ውይይት አደረገ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 15 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ዛሬ ጥቅምት 15 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ 6 ኪሎ በሚገኘው ዋና ጽ/ቤቱ በፌደራሊዝም ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርጓል። በውይይቱ ላይ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አቶ ማሙሸት አማረና የኢትዮጵያዊያን ሀገራዊ ንቅናቄ (ኢሀን) ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና ሌሎች በክብር ተጋባዥነት ተገኝተዋል። በቅድሚያ በየቦታው በአማራ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እና በሌሎችም ወገኖች ጭምር እየደረሰ ባለው ጥቃት ውድ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ለ1 ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደርጓል። በመድረኩ የመግቢያ ንግግር እንዲያደርጉ የተጋበዙት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ስለ ፌደራሊዝም፣አደረጃጀትና አወቃቀር ምን ይምሰል ከማለታችን በፊት የመኖርና ያለመኖር አደጋ የተጋረጠብን መሆኑ ግልፅ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል። ዳሩ ግን ይህ የፌደራሊዝም የውይይት መድረክ ለመማማሪያ ስለሚጠቅም መልካም መሆኑን ጠቅሰዋል። ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ስለ ሀገር ነጻነትና ክብር፣ስለአብሮነት ሲሉ አምባገነናዊ ስርዓትን ከሚታገሉ ወገኖች ጋር ለመታገል ዛሬም እንደ ትናንቱ ምንጊዜም ቢሆን ዝግጁ ነኝ በማለት አረጋግጠዋል። የዳቦ ቆረሳ ስነ ስርዓቱም በመኢአድ ሊቀመንበር በአቶ ማሙሸት አማረ ተከናውኗል። በባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በአቶ ገለታው ዘለቀ የፌደራሊዝም ጽንሰ ሀሳብንና አተገባበርን በተመለከተ ሰፋ ያለ በንፅፅር ላይ የተመሰረተ ማብራሪያ ተሰጥቷል። የትምህርት መድረኩን ላዘጋጀው ባልደራስ፣ጥናቱን ላቀረቡት አቶ ገለታው ዘለቀን፣በመድረኩ በተጋባዥነት ለተገኙት እነ ኢ/ር ይልቃልና ማሙሸት አማረን ባመሰገኑት ተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተው የመወያያ ጥናታዊ ጹሁፍን ያቀረቡት አቶ ገለታው ዘለቀ ምላሽ ሰጥተውበታል። በመጨረሻም ኢ/ር ይልቃል ጌትነት እና አቶ ማሙሸት አማረ በአቶ ገለታው ዘለቀ ለቀረበው ጥናታዊ ጹሁፉና ለአቀራረቡ እንዲሁም የዝግጅቱ ባለቤት የሆነውን ባልደራስን አመስግነው መልዕክት አስተላልፈዋል። ኢ/ር ይልቃል ቀደም ሲል ለመማማር ከጠቀመን መልካም ነው ያሉትን ውይይት እጅግ በጣም ጠቃሚ እና ስርዓቱንና ሀገራችን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በግልፅ ያሳየ የዳሰሳ ጥናት ሆኖ እንዳገኙት በመግለፅ ፓርቲውንና አቶ ገለታውን አመስግነዋል። በብልጭልጭ ነገር የተጠመደና እየተቀያየረ አገር አልባ እያደረገን ያለ ሥርዓት ባለበት ሁኔታ የዜጎች ህይወት እየተቀጠፈ ነው ያሉት አቶ ማሙሸት በዝምታ ውስጥ ያሉ ወገኖች እንዲባንኑ ብሎም ማዕበል እና ጎርፉን በጋራ ሆነው መመከት እንዲችሉ አሳስበዋል። አሁን እየመጣ ያለው እንቅስቃሴ ከብዶናል ያሉት አቶ ማሙሸት በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሪውን መምረጥ አለበት ብለዋል። በዝርዝር የምንመለስበት ይሆናል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply