ባይደን ፑትን ከዩክሬን ጋር ያላቸውን ውጥረት እንዲያረግቡ አሳሰቡ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ትላንት ሀሙስ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቫላድሚር ፑትን ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር “ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ያላትን ውጥረት እንድታረግብ” አሳሰቡ፡፡ 

ይሁን እንጂ 50 ደቂቃ በፈጀው የስልክ ውይይት ቭላድሚር ፑትን በዩክሬን ድንበር አቃራቢያ ያሰፈሩትን ወደ 10ሺ የሚጠጋ ጦራቸውን ሰለማንሳታቸው ምንም የገቡት ቃል የለም ሲሉ አንድ የዩናይትድስ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል፡፡ 

የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ “ሩሲያ ዩክሬንን ብትወር ዩናይትድ ስቴትስና አጋሮችዋ በማያወላዳ መልኩ ምላሽ የምትሰጥ መሆኑን ባይደን ግልጽ አድርገዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አንድ ከፍተኛ የክሬምሊን ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ባይደን ዩናይትድ ስቴትስና አጋሮችዋ ጠንካራ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የሚጥሉ መሆናቸውን በድጋሚ ማስጠንቀቃቸውን ገልጸው የሩሲያው ፕሬዚዳንትም በአጸፋው የራሳቸውን ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ፑትን “እንደዚያ ዓይነቱ እምርጃ በዩናይትድ ስቴትስና በሩሲያ መካከል ያለው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዲበላሽ ያደርገዋል” ማለታቸውንም ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡

የዋይት ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ፣ ሁለቱ አገሮች በሚቀጥለው ወር ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች ለመምክር ሦስት ጊዜ ያህል እንደሚገናኙ ተናግረዋል፡፡ 

ቃል አቀባይዋ ጨምረውም ባይደን በእነዚህ ንግግሮች ውጤት ሊገኝ የሚችለው ነገሮችን ከማባባስ ይልቅ የማርገብን መንገድ በመከተል ብቻ መሆኑን መግለጻቸውን አመልክተዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የመረጃ ባለሥልጣናት ፑቲን በሩሲያና ዩክሬን ድንበር ሠራዊታቸውንን ሲያከማቹ የቆዩ መሆኑን ጠቅሰው ፣ የሳተላይት ምስል መረጃዎች እስከ 100ሺ የሚደርሱ ወታደሮች በአካባቢው መስፈራቸውን ይገልጻሉ ብለዋል፡፡ 

ዩክሬንም እንዲሁ የራሷን ሠራዊት በአካባቢው ማስፈር መጀመሯ ተመልክቷል፡፡

የቀድሞ ሶቭየት ህብረት ግዛት የሆነችው ዩክሬይን ለዓመታት የሰሜን አትላቲክ ቃል ኪዳን ወይም ኔቶ አባል አገር ለመሆን ብትፈልግም ሩሲያ ግን በጽኑ ስትቃወም መቆየቷ ይታወቃል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply