“ቤተ ክርስቲያንን ማፍረስ መንግሥትንና ሀገርን ለማፍረስ የሚደረግ ሙከራ በመሆኑ ይህንን ፈጽሞ መፍቀድ አይገባም”-በኢትዮጲያ የሩስያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ…

“ቤተ ክርስቲያንን ማፍረስ መንግሥትንና ሀገርን ለማፍረስ የሚደረግ ሙከራ በመሆኑ ይህንን ፈጽሞ መፍቀድ አይገባም”-በኢትዮጲያ የሩስያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ የሩሲያ ፌዴሬሽን የፓርላማ (ዱማ) አባላት እና በኢትዮጲያ የሩስያ አምባሳደር አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ ልዑካኑ በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ያላቸውን ክብር፣ አንድነትና ድጋፋቸውን ለመግለጽ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ የሩስያ ፌዴሬሽን የፓርላማ (ዱማ) አባል የሆኑት ሚስተር ኒኮላይ ኖቢችኮ እንደተናገሩት በአሁኑ ጊዜ የሩሲያና የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እያሳለፉ የሚገኙበት ጊዜ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ያጋጠሟቸውን ችግሮች በጋራ በጸሎት ያልፉታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሩሲያ እንደ ሁልጊዜው ሁሉ ሁሉንም ባሕልና ሃይማኖታዊ እሴቶችን በመቀበል ድጋፍ ታደርጋለች፡፡ በተጨማሪም በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ምእመናን ሁሉ ከፈተና እንዲያሳልፋቸው በጸሎት እናስባቸዋለን ብለዋል፡፡ የፓርላማ አባሉ በተጨማሪም እንደገለጹት ቅዱስነታቸውን ሲያገኟቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንና በውይይታቸውም ሀገራቱ ባላቸው ግንኙነትና በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ያለውን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እንደተነጋገሩ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም በሚቀጥለው ሳምንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዑካን በሞስኮ ይገኛሉ ብለን እናስባለን በማለት ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሩሲያ ወንድማማች ሕዝብ እንደመሆኑ መጠን የሚያጋጥሙ ችግሮችንም በቅርብ የሚመለከት እንደሆነ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር የሆኑት ኢቭጌኒ ተርኪሂን ተናግረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማፍረስ መንግሥትን፣ ሀገርን ለማፍረስ የሚደረግ ሙከራ በመሆኑ ይህንን ፈጽሞ መፍቀድ አይገባም፡፡ ነገር ግን ችግሮች ሲፈጠሩ የመጀመሪያቸው ባለመሆኑ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ሰፊው ሕዝብ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ አሁንም ማለፍ እንደሚችል አምናለሁ ብለዋል፡፡ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪሂን አክለው በአሉት ሕጎች፣ መዋቅሮችና እሴቶች በመጠቀም ከመጣው ችግር እንደምትወጡ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምትተዳደርበት የራሷ የሆነ ሕግ የአላት በመሆኑ የተፈጠረውን ችግር በራሷ ሕግና ደንብ መፍታት አለባት ብለዋል፡፡ ዘገባው የማህበረ ቅዱሳን ብሮድ ካስት አገልግሎት ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply