
“ቤታችን ያለምንም ካሳ እና ትክ ሊፈርስ መሆኑ ሲነገረው የአዕምሮ ህመም የገጠመው ባለቤቴ በጅብ ከመበላቱ ለዘመናት የኖርንበትን ቤት በጭካኔ በማፍረስ ሜዳ ላይ ጥለውናል” ስትል በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ባለቤቷ በጅብ የተበላባት እና ቤቷ የፈረሰባት እናት ተናገረች። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ “ቤታችን ያለምንም ካሳ እና ትክ ሊፈርስ መሆኑ ሲነገረው የአዕምሮ ህመም የገጠመው ባለቤቴ በጅብ ከመበላቱ ለዘመናት የኖርንበትን ቤት በጭካኔ በማፍረስ ሜዳ ላይ ጥለውናል” ትላለች አማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ያነጋገራት እናት። የሟች ባለቤት በደቡብ ኢትዮጵያ የዶርዜ ተወላጅ ስትሆን ስሟም ወ/ሮ በቀለች ደጀን ትባላለች። በአዲስ አበባ የካ ክ/ከተማ የወረዳ 5 ነዋሪ ናት። በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ቤታቸው ያለምንም ካሳ እና ትክ ቦታ ሊፈርስ መሆኑ ሲነገረው በድንጋጤ የአዕምሮ ህመም የገጠመው ባለቤቷ አቶ ካሌብ ካኦ ነሃሴ 19/2014 ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ከቤቱ ወጥቶ በቅርብ ርቀት እያለ በጅብ ተበልቶባታል። የሚያሳዝነው ጅቡ ሲበላው የተመለከቱ የጸጥታ አካላትም ሳይፈቀድልን በጥይት አንገድለውም በማለት ግማሽ አካሉን እስኪበላው እየተመለከቱ ነበር ይላሉ ድንጋይ በመወርወር ለማስለቀቅ ጥረት ያደረጉት የዐይን እማኞች። ጅቡም አቶ ካሌብን በመግደል ከራሱ እስከ ወገቡ ድረስ ከበላው በኋላ ተፈቅዷል መባሉን ተከትሎ በጥይት የመገደሉ ዜና ተሰምቷል። በዚህም ከጅብ የተረፈው የባለቤቷ ግማሽ አካል ስርዓተ ቀብሩ በወጉ የተፈጸመ ስለመሆኑ ነዋሪዎች አውስተዋል። ይባስ ብሎ ባለቤቱ ሀዘን ላይ በተቀመጠችበት ለበርካታ ዓመታት የኖረችበት ቤቷ እንዲፈርስ ተደርጎ በጭካኔ ሜዳ ላይ እንድትወድቅ ስለመደረጉ ተገልጧል። ይህ የሆነው በአዲስ አበባ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጫካ ልማት ፕሮጀክት በሚል መነሻ ስለመሆኑ ተመላክቷል። ከየካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ቤታቸው ያለምንም ካሳ እና ትክ ማንነትን ጭምር እየለዩ በተለይም ካለፉት አራት ወራት ጀምሮ እየፈረሰባቸው ያሉ ነዋሪዎች አሁንም ሰሚ አላገኙም፤ ጩኸታቸው ግን እንደቀጠለ ነው። የወገናችን ጉዳይ ያገባናል የሚል ሁሉ እንዲደርስላቸው አሁንም መማጸናቸውን ቀጥለዋል። ከሰሞኑ በለገጣፎ አካባቢ ቤታቸው የፈረሰባቸው እናት ሁለት ልጆቻቸው በጅብ እንደተበሉባቸው፣ አንደኛው ሲሞት ሌላኛው ስለመቁሰሉ መዘገቡ ይታወሳል። በለገጣፎ ድሬ ቀርሳ አካባቢ ሁለት ልጆቿ በጅብ የተበሉባት እናት እንደገና ቀና ብላ ስትመለከት ባለቤቷም በሚያሳዝን መልኩ ራሱን ሰቅሎ ፤ ታንቆ የሞተባት ስለመሆኑ ከሰሞኑ ተዘግቧል።
Source: Link to the Post