ቤት ለማግኘት የሚጠብቁ ነዋሪዎችን አስቆጥቶ የነበረው የቤት ጨረታ፤ አሸናፊዎች ውል መዋዋል ጀምርዋል

ቤት ለማግኘት የሚጠብቁ ነዋሪዎችን አስቆጥቶ የነበረው የቤት ጨረታ፤ አሸናፊዎች ውል መዋዋል ጀምርዋል

ዓርብ ግንቦት 16 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ እና ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ያስገነቧቸውን የመኖሪያ እና የንግድ ቤት ጨረታ አሸናፊዎችን ከትላንትናው እለት ግንቦት 15 ቀን 2016 ጀምሮ ውል መዋዋል ጀምረዋል።

ውል ከተጀመረ ዛሬ ሁለተኛ ቀን የሆነው ሲሆን ከ250 በላይ የጨረታው አሸናፊዎች በወጣላቸው የጊዜ መርሀ ግብር መሰረት በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በመገኘት የክፍያ ማዘዣ እየወሰዱ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ መረጃ ያሳያል።

ለተጨማሪ ንባብ፡ https://addismaleda.com/archives/38042

በቀጣይም የተቀመጠው የውል መዋዋያ የጊዜ መርሀ ግብር ሳያልፍ የጨረታው አሸናፊዎች የሚጠበቅባቸውን መስፈረት በሟሟላት ዘውትር በስራ ቀናት እስከ ምሽት 3:00 ሰአት ድረስ መዋዋል እንደሚችሉ ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።

ይኸው የአዲስ አበባ ቤቶች ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ እና የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ትብብር ከ3 ሺህ የሚበልጡ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን በጨረታ አወዳድሮ ለመሸጥ ያወጣው ማስታወቂያ ለበርካታ ዓመታት ቤት ለማግኘት የቆጠቡ እና እየቆጠቡ የሚገኙ ነዋሪዎችን ማስቆጣቱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን ከሦስት ሺህ በላይ ቤቶችን ለሽያጭ ማቅረቡ ላይ የሕጋዊነት ጥያቄ አንስቶ ነበር።

እንዲሁም ተቋሙ በ1997 ተመዝግበው ከስቱዲዮ እስከ ባለሦስት መኝታ ቤት ድረስ ቤቶች ለማግኘት እየቆጠቡ ያሉ 959 ነዋሪዎች፣ ምን ያህል እንደቆጠቡ የሚገልጽ ሙሉ ስማቸው ከፊርማቸው ጋር ያረፈበትና በድምሩ 144 ሚሊየን 820 ሺህ 085 ብር መቆጠባቸውን ከሚያሳይ ሰነድ በማያያዝ፣ ኮርፖሬሽኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ለመሸጥ የጀመረውን ሒደት እንዲያሳግድላቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ ለዕንባ ጠባቂ ተቋም ጨረታው ይፋ በተደረገበት ዕለት ማስገባታቸው ይታወሳል።

ሆኖም ግን የነዋሪው ቅሬታ እና የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ጥያቄ ምላሽ ባያገኝም ተቋማቱ ጨረታዉን በማወዳደር አሸናፊዎች ውል መዋዋል መጀመራቸውን አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply