ብልፅግና መራሹ መንግስት ከለየለት ደፍጣጭና አምባገነናዊ አካሄድ ሊቆጠብ ይገባዋል ሲሉ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ የምስራቅ ቀጠና ኃላፊ አቶ ታጠቅ አሰፋ ተናገሩ። አማራ ሚዲያ…

ብልፅግና መራሹ መንግስት ከለየለት ደፍጣጭና አምባገነናዊ አካሄድ ሊቆጠብ ይገባዋል ሲሉ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ የምስራቅ ቀጠና ኃላፊ አቶ ታጠቅ አሰፋ ተናገሩ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ኢህአዴግ ህዝብ ዋጋ ከፍሎ ያመጣውን የለውጥ ጭላንጭል ሙሉ በሙሉ ጨለማ እያለበሰው መሆኑን የገለፁት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መኢአድ የምስራቅ ቀጠና ኃላፊ አቶ ታጠቅ አሰፋ ኢህአዴግ ልክ ዘንዶ ቆዳውን ቀይሮ እንደሚታደሰው ሁሉ በብልፅግና ስም ቆዳውን ቀይሮ ፍፁም አምባገነንና አፋኝ የሆነ አዋወቃቀር ይዞ መምጣቱን ተረድተናል፤ ይህ ደግሞ የትም አያደርስም ብለዋል። ህዝብ ቢታፈንም መቼም ቢሆን ተሸንፎ አያውቅም ያሉት አቶ ታጠቅ ይህም ከዚህ በፊት ተሞክሮ የተረጋገጠ እውነታ ነው ሲሉም አክለዋል። ዛሬ መቀሌ ላይ የመሸጉት የኢህአዴግ አሰልጣኞችን ህዝብ ባደረገው ተጋድሎ እንዴት እንደሸኛቸውና ትናንት ሲናገሩት የነበረው መዘንጋቱ የብልፅግናው መሪ እንደሚሉት ህዝብ ሳይሆን ስርዓቱ ምን ያህል በሾርት ሜሞሪ ውስጥ መሆኑን አመላካች ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። አሁን እየተሄደበት ያለው የአፈና መንገድ ለማንም የማይበጅ በመሆኑ ብልፅግና ቆም ብሎ ቢያስብበት ነው የሚሻለው ያሉት አቶ ታጠቅ በህዝብ ዘንድ ብዙ ጥያቄ የተነሳበትን ህገ መንግስት እንኳ በግልፅ እየጣሱት እንደሚገኙ ነው አክለው የተናገሩት። ከሰሞኑ አብን የጠራው ህዝባዊ ሰልፍ እንዳይደረግ ብልፅግና ህገ መንግስቱን በመጣስ ያሳየው የክልከላ አካሄድ ፍፁም አምባገነናዊ መሆኑን ነው አቶ ታጠቅ አፅኖት ሰጥተው የገለፁት። ይህ አካሄድ የሚያሳየው ተሰሚነት ያላቸውን ሰዎች በማሰር የህዝቡን የልብ ትርታ እየለካ ያለ በእብሪት የተሞላ ስርዓት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ታጠቅ በተለይ በራያ ቆቦ ላይ የተደረገውን ፍፁም ሰላማዊና ጨዋነት የተሞላበት ሰልፍ ሊመሰገን ሲገባው ብልፅግና ለምን እንዳናደደው አልገባኝም ብለዋል። ሰልፍ በመከልከል አገር ይፈርሳል፤ለውጥ ይደናቀፋል፤ ወቅቱ የኮሮና ነው የሚለው ምክንያት ሚዛናዊነት የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው ያሉት አቶ ታጠቅ አዲስ አበባ፣ሀረር፣ጅማ ላይ የተደረጉ ሰልፎችን በማስታወስ ለብልፅግና ሲሆን ኮሮና አይሰራም፤ ለተቃዋሚዎች ሲሆን ኮሮና ይሰራል የሚለው ማንንም የማያሳምን መንግስታዊ ጉርምስና ስለሆነ ቢቀር መልካም ነው ሲሉ መክረዋል። ከህወሀት በባሰ መልኩ እየሄዱ አያ ጅቦ መጣብህ እያሉ ህዝብን ለመሸወድ የመሞከር ማንአለብኝ አካሄድን ትተው ቁጭ ብለው መምከሩ ይሻላቸዋል ሲሉ ያሳሰቡት። ባህር ዳርና ሌሎች ከተሞች ላይ በተደረገው የሰልፍ እንቅስቃሴ ላይ የታየው የስርዓቱ አፈና፣ ክልከላና የመሳሪያ ውደራ አሁንም በአፈሙዝ መታበይና መተማመን ተባብሶ መቀጠሉን ያሳያል፣ ምርጫውንም ለማፈን ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ይመስላል ነው ያሉት። ከመኢአድ የምስራቅ ቀጠና ኃላፊ ከአቶ ታጠቅ አሰፋ ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ያደረግነውን ቆይታ በአሚማ የዩቱብ አድራሻ የምናጋራ ይሆናል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply