ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮችን ከምክር ቤት በኃይል ማገዱን እንዲያቆም ተጠየቀ

አርብ ግንቦት 11 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በሕዝብ ተመርጠው በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት የገቡ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባላትን፤ ከምክር ቤቱ በኃይል ማገዱን እንዲያቆም ፓርቲው ጠየቀ፡፡

የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፊ ኃላፊ ባንዲራ በላቸው፤ <<ገዥው ፓርቲ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው የቁጫን ሕዝብ በክልሉ ምክር ቤት የወከሉ አባላትን ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ መንገድ መታገዳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፎባቸዋል።>> ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

<<ይህን ጉዳይ በዋናነት እያስፈጸሙ ያሉት የክልሉ ምክር ቤት ተጠሪ እና የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ጥላሁን ከበደ ናቸው።>> የሚሉት ባንዲራ፤ <<ሰውዬው የጋሞ ዞን አስተዳዳሪ በነበሩበት ወቅትም የቁጫ ሕዝብ እንዲጠፋ ሲሰሩ የኖሩ ናቸው።>> ብለዋል፡፡

ስለሆነም ምክር ቤቱን በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ በመግለጽ፤ የታገዱት አባላት ምክር ቤቱ ተወያይቶ ውሳኔ ሳይሰጥበት ከህግ አግባብ ውጭ በአፈጉባኤው መታገዳቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደተጻፈባቸው ገልጸዋል፡፡

<<የምክር ቤት አባላት ከምክር ቤቱ የሚታገዱት ከባድ ወንጀል ሰርተው ያለመከሰስ መብታቸው ሲነሳ ወይም የሥራ ዘመናቸው ሲያበቃ ብቻ ነው።>> ያሉት ኃላፊው፤ ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ታግደዋል የታባሉት ሦስት የቁጫ ሕዝብ ተወካዮች በዚህ አግባብ አለታገዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት ግንቦት 01/2015 በጻፈው ደብዳቤ፤ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን በመወከል የምክር ቤቱ አባል የነበሩ ጌዲዮን ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ማሳሞ ማዳልቾ እና ሊዲያ በለጠን ከምክር ቤቱ መሰረዛቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡

ምክር ቤቱ ሦስቱ ተወካዮች የታገዱበትን ምክንያት ሲጠቅስ፤ <<የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በቁጫ ምርጫ ክልል ምርጫ እንዲደገም ውሳኔ ቢሰጥም ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ላለማስፈጸም ያቀረበው ምክንያት ህግን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ ድጋሜ ምርጫ ማካሄድ በማስፈለጉ ነው።>> ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያ ፓርቲ በምርጫ ክልሉ ምርጫ እንዲደገም የሚያስገድድ ነገር አለመኖሩን በመጥቀስ፤ መንግሥት በቁጫ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ የመብት ጥሰት እየፈጸመ ነው ሲል በተደጋጋሚ ክስ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

The post ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮችን ከምክር ቤት በኃይል ማገዱን እንዲያቆም ተጠየቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply