ብሔራዊ ሎተሪ አድማስ የተሰኘ የሎተሪ ትኬትን በዲጅታል አማራጭ ማቅረቡን አስታወቀ

አርብ ሐምሌ 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ብሔራዊ የሎተሪ አስተዳደር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር አድማስ የተሰኘ የዲጅታል ሎተሪ መጀመሩን የገለጸ ሲሆን፤ አገልግሎቱን በቴሌብር እና በ605 አጭር የጽሁፍ መልዕክት ማግኘት እንደሚቻልም አስታውቋል።

የብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር እና ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ሎተሪ ለመጀመር የሚያስችል ሥምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።

የተቋማቱ ሥምምነትም የብሄራዊሎተሪ አስተዳደር ከዚህ በፊት ለህትመት እና ሌሎች ተያያዥነት ላላቸው ሥራዎች ያወጣው የነበረውን ወጪ በከፍተኛ ኹኔታ ለመቀነስ ያስችላል ተብሏል።

ተቋሙ ከዚህ በፊት በወረቀት ትኬት ብቻ ሲያካሂደው የነበረው የሎተሪ ሽያጭ ከህትመት ጀምሮ እስከ ሥርጭቱ ድረስ ረዥም ሂደት የሚወስድ የነበረ ሲሆን፣ ዲጅታል የሎተሪ ሥርዓቱ ግን ቀልጣፋና በአጭር ጊዜ ለኹሉም ሰው በሞባይል ተደራሽ መሆን የሚያስችል እንደሆም ተነግሯል።

በቅርቡ ይወጣል የተባለውና “አድማስ” የተሰኘውን የዲጂታል ሎተሪ ትኬትም ደንበኞች፤ በቴሌብር አጭር ቁጥር 127 በመደወል፣ እንዲሁም ወደ 605 ላይ A ብለው ወይም ማንኛውንም ፊደል አስገብተው በአጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ መግዛት ይችላሉም ተብሏል፡፡

ብሔራዊ የሎተሪ አስተዳደር በ2022 በቴክኖሎጂ የዘመኑ የዕድል ጨዋታዎችን በማስፋፋት የላቀ ገቢ ለማግኘት ማቀዱንም አስታውቋል።

ተቋሙ በ25 ዓመት ብቻ ለሎተሪ አዟሪዎች ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ እንደከፈለ በማውሳትም፤ ዲጅታል ሎተሪው ከወረቀት ዋጋ ጀምሮ ወጭ ቆጣቢ ከመሆኑም በላይ ከእንግዲህ ለሎተሪ አዟሪ የሚከፈል ወጭን እንደሚያስቀር ነው የተነገረው።

ዲጅታል የሎተሪ ሥርዓቱ ብሔራዊ የሎተሪ አስተዳደር ለ60 ዓመት ደንበኞቹ አገልግሎቱን በቀላሉና በሰፊው ለማድረስ እንደሚያስችለው የተገለፀ ሲሆን ከ63 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞችን ተደራሽ እንደሚያደርግም ተመላክቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply