ተመስገን ደሳለኝ አልተለቀቀም

https://gdb.voanews.com/F8A676BC-529E-461B-8CE1-D49E4B4D3049_w800_h450.jpg

ታስሮ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ30 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈታ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ዛሬ ቢወስንም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሊለቅቀው ፍቃደኛ አለመሆኑን ጠበቃውና ወንድሙ ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል፡፡ 

ቀደም ሲልም ይኸው ችሎት ተመስገን በ100 ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቅ ወስኖ የነበረ ቢሆንም ዓቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ ሳይፈታ መቆየቱ ታውቋል፡፡  

ወንድሙ አቶ ታሪኩ ደሳለኝ ወደ ማረሚያ ቤቱ ሄደው እንደነበረና ማረምያ ቤቱ የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቢደርሰውም “አይፈታም” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ገልፀዋል። 

ማረሚያ ቤቱ ያልለቀቀበትን ምክንያት የደሳለኝ ጠበቃ አቶ ቤተማርያም አለማየሁ ሲናገሩ ቀደም ሲል ከፍርድ ቤት ጋር በተለዋወጧቸው የፅሁፍ ሰነዶች የሚያውቀው ጉዳዩ ‘የሽብር ጉዳይ’ የነበረ መሆኑን መጠቆሙንና ዛሬ ተፅፎ የደረሰው የተለየ በመሆኑ እንደሆነ ማሳወቁን ገልፀው “’ፍርድ ቤቱን ማብራሪያ እንዲሰጠኝ በደብዳቤ እጠይቃለሁ’ ብሏል” ብለዋል፡፡  

ሆኖም “’የሽብር ጉዳይ የተባለው ነገር ማረምያ ቤቱ ያመጣው አዲስ ነገር ነው” የሚሉት አቶ ቤተማርያም በፍርድ ቤትና በማረምያ ቤቱ መካከል እንዲህ ዓይነት መፃፃፍ እንዳልነበረ ተናግረዋል። 

ክሱ “ወታደራዊ ምሥጢሮችን ለህዝብ መግለፅ እየተባለ መቆየቱንና ለደንበኛቸው ሲከራከሩ የነበረውም በዚሁ የክሥ ጭብጥ ጉዳይ እንደነበረ አመልክተዋል። 

ከፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አስተያየት ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው። እስካሁን አልተሳካም፤ ምላሽ ለማግኘት ጥረታችንን እንቀጥላለን። 

 

Source: Link to the Post

Leave a Reply