ተማሪ ቢንያም ኢሳያስ የህክምና ትምህርቱን እንዲቀጥል ተወሰነ

አርብ ሐምሌ 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ቢንያም ኢሳያስ የህክምና ትምህርቱን እንዲቀጥል መወሰኑን አስታውቋል።

የተማሪ ቢንያም ኢሳያስን ትምህርት በተመለከተ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና የሕክምና ት/ቤት ለተማሪው የትምህርት ሂደት ይረዳሉ ያሏቸውን አማራጮች ማቅረባቸው ይታወሳል።

ሆኖም ተማሪ ቢንያም ብቸኛ ፍላጎቱ የሕክምና ትምህርትን መማር እንደሆነ ገልጿል።

በዚሁም መሠረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የጤና ሳይንስ ኮሌጅ አካዳሚክ ኮሚሽን በጋራ ባካሄዱት ስብሰባ ተማሪ ቢንያም ኢሳያስ የሕክምና ትምህርቱን እንዲቀጥል ተወስኗል።

እስካሁን የተቋረጡ ትምህርቶችንም በማካካስ ትምህርቱን ካቆመበት እንዲቀጥል ይደረጋል መባሉን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

ምንም እንኳን የትምህርት ሂደቱ ከባድ እና ውስብስብ ቢሆንም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና የሕክምና ት/ቤቱ የተማሪ ቢንያምን ትምህርት የተሳካ እንዲሆን የሚችሉትን ኹሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተገልጿል።

ተማሪ ቢኒያም ከልጅነቱ አንስቶ በትምህርቱ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበና፤ የልጅነት ህልሙ የሆነውን ህክምና ትምህርት ለመከታተል ወደ ጥቁር አንበሳ በመግባት 4 ዓመት ድረስ የህክምና ትምህርት (ሜዲስን) በከፍተኛ ውጤት የተማረ ሲሆን፤ የአራተኛ ዓመት ተማሪ እያለ የአካል ጉዳት እንዳለበት በዩንቨርስቲው በመታወቁ፤ ዩኒቨርሲቲው ላለፉት ስምንት ወራት ጉዳዩን ይዞ ሲመረምር መቆየቱ ይታወቃል፡

ኮሌጁ ባዋቀረው ኮሚቴ በቀረበለት ምክረ ሀሳብ መሰረትም፤ ተማሪ ቢንያም ከጤና ትምህርት ጋር ተያያዥነት ካላቸው ትምህርቶችን ውስጥ፤ በህክምና ፋርማሲ፣ በህክምና ላብራቶሪ ሳይንስ እንዲሁም በህክምና ላቦራቶሪ በመረጠው ዘርፍ እንዲማርና ባችለር ኦፍ ባዮሜዲካል ሳይንስ እንዲሰጠው ኮሚቴው ወስኖም እንደነበር ይታወሳል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply