ተማሪ ፅጌረዳ ግርማይን በስለት ወግቶ የገደለው ተማሪ በ22 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የውሳኔ ማሻሻያ አደረገ

የጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም ተከሳሹ በ17 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል

አርብ ጥቅምት 11 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የነበረችውን ተማሪ ፅጌረዳ ግርማይን በስለት ወግቶ የገደለው ተማሪ በ22 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የውሳኔ ማሻሻያ አድርጓል።
የጋሞ ዞን ፍትህ መምሪያ ኃላፊ ሽመልሰ ጮራ እንደገለፁት፤ የወንጀሉ አድራጊ እና ተደራጊ ቀደም ሲል የአርባምንጭ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ተከሳሽ ብሩክ በላይነህ “ያቀረብኩትን የፍቅር ጥያቄ አልተቀበለችም፣ ሌላ ፍቅረኛ ይዛ ውጪ ልትወጣ ነው።” በሚል ስሜት ተነሳስቶ የተማሪ ጽጌረዳ ግርማይን አካል ዘጠኝ ጊዜ በስለት ወጋግቶ የመግደል ወንጀል ፈፅሟል።
በቀድሞው አጠራር የጋሞ ዞን ዐቃቤ ህግ የመሠረተውን የወንጀል ክስ ተመልክቶ ግራና ቀኙን ሲያከራክር የቆየው የጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀደም ሲል በቀን 19/10/2014 በዋለው ችሎት በተከሳሽ ላይ የ17 ዓመት ፅኑ እስራት ቅጣት መወሰኑም ይታወቃል።
የዞኑ ዐቃቤ ህግ በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር በመሰኘቱ ይግባኙን ለደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርቦ ሲከታተል መቆየቱን ሽመልስ ተናግረዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበኩሉ የጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የበየነው የቅጣት ውሳኔ ከተፈፀመው ወንጀል አኳያ ተገቢነት ያለው ሆኖ ባለመገኘቱ፤ የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አሻሽሎ ሰሞኑን በዋለው ችሎት በተከሳሽ ላይ የ22 ዓመት ፅኑ እሥራት የቅጣት ውሳኔ ማሰተላለፉን ሽመልስ ገልጸዋል ሲል የጋሞ ዞን መ/ኮሚዩኒኬሽ አስታውቋል።

The post ተማሪ ፅጌረዳ ግርማይን በስለት ወግቶ የገደለው ተማሪ በ22 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የውሳኔ ማሻሻያ አደረገ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply