You are currently viewing ‹‹…..ተስፋ ቆርጬ የመሸነፍ ስሜት ተሰምቶኝ ነበረ።››          ~  እሸቱ መለሰ  የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ እሸቱ፣ በስታንዳፕ ኮሜዲዎቹ በስፋት በተመልካች ዘንድ…

‹‹…..ተስፋ ቆርጬ የመሸነፍ ስሜት ተሰምቶኝ ነበረ።›› ~ እሸቱ መለሰ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ እሸቱ፣ በስታንዳፕ ኮሜዲዎቹ በስፋት በተመልካች ዘንድ…

‹‹…..ተስፋ ቆርጬ የመሸነፍ ስሜት ተሰምቶኝ ነበረ።›› ~ እሸቱ መለሰ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ እሸቱ፣ በስታንዳፕ ኮሜዲዎቹ በስፋት በተመልካች ዘንድ ይታወቃል። በቴሌቪዥን እና በሬድዮ አቅራቢነት እንዲሁም በዩቱብ ቻናሉ የተለያዩ ይዘት ያላቸው መሰናዶዎች አዘጋጅ እና አቅራቢ ነው። እሸቱ መለሰ የሀገራችንን የስታንዳፕ ኮሜዲ አንድ እርምጃ ያራመደ ወጣትም ነው። ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ባለፉት 4 ወራት ከ100 በላይ የመዝናኛ፤ የጥበብ እና የመረጃ ሰዎችን ግለታሪክ ሲያወጣ ነበር። አሁን ደግሞ የኮሜድያን እሸቱ መለሰን ግለ ታሪክ እንደዚህ ሰንዶታል። ትውልድ ልጅነት እና ትምህርት ገና ትንሽ ሆኖ ነጠላውን አጣፍቶ ከፒኮክ ወደ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን ሲኳትን በልቡ ሰንበት ት/ቤት ያጠናውን መዝሙር እየደጋገመ ነበር፡፡ አዳማ ለዚህ ወጣት ያጨበጨችው ዛሬ በተለያዩ የቲቪ መስኮቶች ላይ ተመልክታው አልነበረም፡፡ እሸቱ መለሰ አዳማ ነው ተወልዶ ያደገው። ሰንበት ት/ቤትና አፄ ገላውድዮስ ት/ቤት እሸቱ እንዲህ ይላል ‹‹….ቤተ -ክርስትያን ጠፍጥፋ ሠርታኛለች፡፡ አስታውሳለሁ 9ኛ ክፍል አንድ ልጅ ቤተ- ክርስትያን እንሂድ ብሎ ናዝሬት ገብርኤል ፈለገ ሠላም ሠንበት ት/ቤት አስመዘገበኝ ። ብዙ ነገር ተማርኩኝ፡፡ የመጀመሪያ የህይወት ፈተናም ቢሆን የቀመስኩት እዚያው ነው፡፡ ›› ይላል እሸቱ መለሰ፡፡ ቤ/ክርስትያኗ ሁለት አመታዊና እጅግ ደማቅ በአላት ነበሯት፤ ከእነዚህ መካከል ታህሳስ እና ሀምሌ 18 ማለትም የገብርኤል ዋዜማ በሰንበት ት/ቤቱ የሚቀርብ ዝግጅት አለ። ዝግጅቱ ግጥም፣ ዜማ፣ ድራማና ስነፅሁፍ ይቀርብበታል፡፡ ታዳሚው እጅግ ብዙ ነው። መድረክ ላይ የሚወጡት ደግሞ ከህፃናቱ ጀምሮ በጣም የበሰሉ ስራዎችና ከፍተኛ ዝግጅት ነበር፡፡ እና የሀምሌው ዝግጅትን ለማቅረብ እሸቱ ለአንድ ገፀ- ባህሪይ እጩ ተደርጎ ማጥናት ጀመረ። በርትቶ አሁ፤ ከእሸቱ ጋር እንዲያጠና የተመደበው ልጅ ደግሞ ነባርና በጣም ጎበዝ ነበር። ትዝታውን ሲያስታውስ እሸቱ እንዲህ ይላል ‹‹…. ከኔና ከሱ የተሻለው ሠው ሀምሌ 18 ሌሊት እንደ አሸዋ በተበተነው ምዕመን ፊት ይቀርባል፡፡ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ውስጥ ተገባ፡፡ ተፎካካሪዬን በአምስት ወር ጭንቅ ውስጥ መክተቴ እራሱ አስደስቶኛል። አይደርስ የለምና ቀኑ ቀረበ፡፡ ሀምሌ 18 ቀን ከሰዐት በመዝሙር እና ስነ ፅሁፍ ክፍል ተጠርቼ አድናቆት ተሰጠኝ፡፡ ፀባዬ ሸጋ መሆኔም ተመሠከረልኝ፡፡ ሆኖም ደባልህ በልምድ ስለሚበልጥህ ዛሬ ድራማ እንዲያቀርብ እሱን መርጠነዋል አሉኝ፡፡ መጀመሪያ ላይ ሲጠሩኝ ለራሴ የነገርኩት እኔ ባልመረጥም ሊከፋኝ እንደማይገባና እዚህ የመጣሁት ከራሴ አስበልጬ ወንድሜን መውደድ እንዳለብኝ ነበር። ሆኖም ሁለቱ ሀላፊዎች እንዳልተመረጥኩ ሲነግሩኝ መርዶ መሠለኝ፡፡ ሠዎቹን ከተለየሁ በኋላ ንዴቴን መቆጣጠር አቅቶኝ የቤ /ክርስትያኑን ቅጥር ግቢ ጥዬ ወጣሁ፡፡ ሆኖም እራሴን ተቆጣጥሬው ተመልሼ ለሊቱን ወዳ አሳደገኝ ቤት ተመልሼ ዝግጅቱን ታደምኩ፡፡ እንዲያውም በሰንበት ት/ቤታችንን የቀረበው ዝግጅት አስደስቶኝ ለሚቀጥለው አመት በሚገርም ብቃት እንደምመጣ ቃል ገባሁ፡፡ የሆነውም እንዲያ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ድራማ በማቅረብ ብቻ ሳይሆን እስከመጻፍም አስተዋፅኦዬ አደገ፡፡ ጭራሽ ተፎካክረን ያሸነፈኝንም ስድ ንባብ ፅፌ አለም ሰፊ መሆኗን አብረን ተውነን አሳየን፡፡ ፈረንጅ እንደሚለው ‘ ላያችን ላይ የዘጉብንን በር ህንፃውን ገዝተን እናሳያቸዋለን፡፡’ አይነት መሆኑ ነው፡፡ ይህን ልምድ 11ኛ ክፍል ታሪክ ላይ ተጠቀምኩት፤ መምህራችን የአፄ ቴዎድሮስን፣ አሉላ አባነጋን፣ የአፄ ዮሀንስና የጀግኖቻችንን ታሪክ በድራማ መልክ እንድናቀርብ አዘዘን። የኔ ቡድን ተማሪዎችን የሰንበት ት/ቤት ልምዴን ተጠቅሜ ከጥናት እስከ ገፀ ባህሪይ ምደባ ተሳትፌ የድራማው ቀን ከክፍላችን አንደኛ ወጣን፡፡ ሌሎች የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ብዙዎቹ እንዳስጠናቸው ጠይቀውኝ ረድቻቸዋለሁ። የስራ ህይወት ጅማሮ እሽቱ መለሰ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2004 ዓ.ም ከተመረቀ በኋላ ህይወት ለሱ አልጋ ባልጋ አልነበረችም። በቴአትር ጥበባት ዲግሪውን ከያዘ በኋላ እንዳሰበው ቴአትር ቤቶቹ ወይም የፊልም ኢንዱስትሪው ብሎም የመዝናኛው አለም አዲስ መጤን የሚጋብዙ አልነበሩም፡፡ ነገሮች የተቆላለፉ በዝምድናና በመተዋወቅ የሚሰሩ ነበሩ ይላል እሸቱ። እሸቱ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ሲያስታውስም ‹‹…..ከተመረቅሁ በኋላ ያሉት ሶስት አራት አመት እጅግ ከባድ እና ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ፡፡ የግሌን የማስታወቂያ ድርጅት ከእህቴ ባል ጋር ከፈትን። ግን እንደታሰበው አዋጭ አልነበረም፡፡ ስራዎች የሚሰሩት በመተዋወቅ ነበር። ቤት ተከራይተን ንግድ ፍቃድ አውጥተን ባዶ ቤት ታቅፎ መዋል የተለመደ ሆነ፡፡ ከኔ አልፎ እህቴንም የእህቴ ባልንም እንዳከሰርኩ ተሰማኝ። ያኔ ከባድ ጭንቀት ውስጥ ገብቼ ነበር፡፡ እንደማልጠቅም እና ለምን እንደተፈጠርኩ አማርር ነበር። ቤቴን ዘግቼ መዋል ጀመርኩ፡፡ የተሰላቸና ተደጋጋሚ ቀኖች እና ህይወት መምራት ጀመርኩ። አንድ ቀን ማለዳ ግን ነገሮች ተለወጡ፡፡ ማማረሬን ተውኩት፡፡ ሰው አድርጎ ነው የፈጠረኝ፡፡ አሞራ ወይ ዋሊያ ወይ ደግሞ ሸለምጥማጥ አድርጎ አይደለም የፈጠረኝ፤ ሰው ነኝ ባምሳያው በመልኩ መተንፈስ ምችል፣ማውራት፣መራመድ፣መቆም መተኛት የምችን ወጣ ብዬ ደም ብለግስ ያንዲት ወላድ እናትን ነብስ ማዳን የምችል ሰው ነኝ። ያኔ ማለዳ መነሳት ጀምርኩ፤ ከፀሀይዋ ጋር ሰዎችን ማግኘት ጀመርኩ ስለ ስራ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ማውራት ጀመርኩ፡፡ ያኔ ነበር የየኛ ፕሮግራምን መድረክ ለመምራት የታጨሁት፡፡ ገርል ኢፌክት ግሎባል (girl effect global) ከተባለ ተቋም ጋር። 11 መድረኮች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወርን አቀረብን፡፡ አዘጋጆቹም ተመልካቹም ልብ ውስጥ ለመግባት ቻልኩ፡፡›› ይላል አሸቱ መለሰ። በየኛ የሬድዮ ፕሮግራም ለአመታት በአቅራቢነት ሰርቷል በ2010 ዓ.ም በአይነትም በአቀራረብ ከፍ ያለ ስታንዳፕ ኮሜዲ ለመድረክ አበቃ፡፡ ያኔ እሸቱ በደንብ ህዝብ ውስጥ መግባት ቻለ፡፡ የሱን መድረኮች ለመሳተፍ ረጃጅም የተመልካች ሰልፎች መታየት ጀመሩ። ከ7 በላይ የሙሉ ስአት እና ስታንዳፕ ኮሜዲዎችን ለመድረክ አብቅቷል። በ2012 ዓ.ም መስከረም ወር እሸቱ በተመልካች ድምፅ ተመርጦ በኢቢኤስ ቴለቪዥን ጣቢያ የሚተላለፈውን የቤተሰብ ጨዋታ የተሰኘውን ፕሮግራም ማቅረብ ጀመረ፡፡ በዛም የተመልካች አድናቆትንና ክብርን ማትረፍ ችሏል። በአሁኑ ሰአት እሸቱ ዶንኪ ዩቲዩብ የተሰኘ የዩቲዩብ ቻናል ያለው ሲሆን ከ500,000 በላይ ሰብስክራይበር ያለው ቻናል ነው። በወር ከ6,000,000 ሚሊየን በላይ ሰዎች ይከታተሉታል 40 ዝግጅቶችን በወር ለተመልካች ያደርሳል። ዶንኪ ዩቲዩብ የመረጃና የመዝናኛ ዝግጁቶችን እና የበጎ አድራጎት ቪዲዮዎችን ይለቃል፡፡ በበጎ አድራጎት ስራዎቹ እስካሁን 50 ሚሊየን ብር አሰባስቦ ለተቸገሩ እናቶች እና ለታመሙ ህፃናት፣ወጣቶች እንዲሁም ለመስኪዱና ቤተክርስቲያን መስጠት ችሏል። ዶንኪ ዩቲዩብ በቋሚነት ለ21 ወጣቶች የስራ እድልም ፈጥሯል። እሸቱ መለሰ በቅርብ የሚያውቁት ለስራው ያለውን ፍቅር እና ትጋት በተለይም ቡድን በማዋቀር እና የስራ ክፍፍልን በመስጠት ለተለያዩ ወጣቶች የስራ እድልን መፍጠሩ እንደሚያስገርማቸው ይናገራሉ። እሸቱ ስራዎች በቡድን ሲሰሩ ጠንካራ ይሆናሉ የሚል እምነት አለው፡፡ በተጨማሪም ባልደረቦቹ ስራቸውን ወደውት እንዲሰሩ እና የአለቃ እና የሰራተኛ ስሜት እንዳይሰማቸው ማድረግ ላይ ጎበዝ ወጣት ነው፡፡ የተሻለ ገቢ እንዲኖራቸውም ይጥራል፡፡ ከዚያ በዘለለ ለስራው ትጉህ መሆኑን የሚያሳየው ከሚያቀርባቸው መድረኮች በፊት የሚያደርጋቸው ተደጋጋሚ ሙከራዎች እና አስተያየት የሚሰበስብበት መንገድ ነው፡፡ የኮሜዲ ስራዎቹ ለህዝብ ከመቅረባቸው በፊት በቅድሚያ የተመረጡ ሰዎች ተመልክተውት አስተያየት ይሰጡታል ይቀበላል፡፡ ከዚያ ውጭ የግል ስብእናው ደግሞ ይበልጥ የሚያስደስት ነው፡፡ ሰው ያከብራል፡፡ ለማገዝ ይጥራል፡፡ በአንድ ወቅት እሸቱ መለሰን አንድ የታመመ ወጣት በዩቲዩብ ቻናሉ እርዳታ እንዲያገኙ እንዲረዳው የጠየቀው ጋዜጠኛ እሸቱ የመለሰለትን እንዲህ ያስታውሳል። በአንድ ወቅት ለአንድ ወንድማችን የገቢ ማሰባሰቢያ እያደረግን በርሱ የዩትዩብ ቻናል ማስታወቂያ እንዲሰራልን ብቻ ጠየቅኩት፡፡ በሰዓቱ በርካታ ወገኖች በቻናሉ ፕሮግራም እንዲሰራላቸው እና እርዳታ እንዲደረግላቸው ወረፋ አስይዘው ነበር፡፡ በዚህም ተራው እስኪደርሰው የግሌን ከአስራት በኩራቴ ላይ ልለግስ በሚል ቼክ ፅፎልናል፡፡ ከገንዘቡ በላይ የተናገረው ንግግር አስገራሚ ነበር፡፡ ይህ የኔ ገንዘብ አይደለም ይህ የዋህ ህዝብ ነው የሰጠኝ፡፡ ስለዚህ የተሰጠኝን መልሼ ሰጠሁ እንጂ ምንም የፈጠርኩት ነገር የለም ነበር ያለኝ፡፡ ይህ ያለውን ትህትና እና ፈሪሃ እግዚአብሔር የሚያመላክት ነው፡፡ መዝጊያ ÷ እሸቱ መለሰ የስታንዳፕ ኮሜዲ ስራውን በጥናት ላይ ብቻ ተመስርቶ ያከናውናል፡፡ በዶንኪቲዩብ የሚቀርባቸው መሰናዶዎች ብዙዎቹ የማነጽ አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ እሸቱ ከተመረቀ 10 አመት ይሞላዋል፡፡ በዚህ 10 አመት ጊዜ ውስጥ በበርካታ ውጣ ውረድ አልፎ ዛሬ ላይ መድረስ ችሏል፡፡ እሸቱ በህይወቱ ስኬትን ሲፈልግ ነበር፡፡ ዛሬ እሸቱ በአንድ በኩል ስራ ፈጣሪ ነው ፡፡ ደግሞ በሌላ መልኩ የኪነጥበብ ሰው ነው፡፡ እሸቱ ወጣቱን ትውልድ ወክሎ ፤ የሚድያ ዘርፉን ወክሎ ጥሩ ተምሳሌት መሆን የሚችል ነው፡፡ እነሆ አጠር አድርገን አዲሱ ትውልድ እንዲያውቀው ታሪኩን አቅርበናል፡፡/ የዚህ የዊኪፒዲያ ጽሁፍ የምርምር እና የጽሁፍ ስራ የተከናወነው በናትናኤል ሲሳይ ነው፡፡/ (ተወዳጅ ሚድያ) “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply