በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት የህዳሴዉ ግድብ ሶስትዮሽ ድርድር እንዲሁም የኢትዮ ሱዳን የድንበር ዉዝግብ በሠላማዊ መንገድ ሊፈታ ይገባል ብለዋል፡፡
ቱርክ ከሱዳን እና ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ያላት አገር መሆኗን የገለፁት አምባሳደሯ፤ ጦርነት ለሁለቱም አገራት ስለማይበጅ ልዩነታቸዉን በዉይይት እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
አምባሳደር ያፕራክ አልፕ አገራቸዉ በየትኛዉም ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም አስታዉቀዋል፡፡
አገራቸዉ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ ልዉዉጥ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እንደምትሰራም ነዉ አምባሳደሯ ያስታወቁት፡፡
ቱርክና ኢትዮጵያ በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸዉ የገለፁት አምባሳደር ያፕረክ አልፕ፤ አሁን ላይ የአገራቱ አመታዊ የንግድ ልዉዉጥ 6 መቶ ሚሊዮን ዶላር ደርሷል ብለዋል፡፡
በቀጣይም የንግድ ልዉዉጡን ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዉ በቅርቡም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሁለቱን አገራት ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ከአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር መምከራቸዉንም አስታዉሰዋል፡፡
አሁን ላይ ከ2መቶ 20 በላይ የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙና ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ማድረጋቸዉን ያስታወቁት አምባሳደር አልፕ ለ25 ሺህ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠሩም ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በትምህርት ዘርፍ በ የአመቱ ለ75 ኢትዮጵያዉያን የትምህርት ዕድል እንደምትሰጥም አንስተዋል፡፡
በአጠቃላይ የቱርክ መንግስት በኢንቨስትመንት፤ በቴክኖሎጂ ልዉዉጥ፤ በሰብኣዊ እርዳታ በቱሪዝምና በሌሎችም ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አምባሳደሯ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በአባቱ መረቀ
ሰኔ 03 ቀን 2013 ዓ.ም
Source: Link to the Post