ቱኒዚያዊያን በመንግስት ላይ የጀመሩት ተቃውሞ ከአራት ቀናት በላይ አስቆጥሯል::

አዲስ አበባ፣ጥር 12፣ 2013 ቱኒዚያዊያን በመንግስት ላይ የጀመሩት ተቃውሞ ከአራት ቀናት በላይ አስቆጥሯል:: ተቃዋሚዎቹ ጎዳናዎችን በመዝጋትና ቁሳቁሶችን በእሳት በማቀጣጠል ቁጣቸው በአደባባይ ሲያሰሙ ታይተዋል፡፡ የተቃውሟቸው መነሻ በሀገሪቱ የተንሰራፋው ድህነትና የስራ አጥነት መባባስ መሆኑን ለተቃውሞ በወጡበት ወቅት ገልፀዋል፡፡

አልጀዚራ በዘገባው እንዳስነበበው ሰልፈኞቹ የተለያዩ ሱቆችንና የንግድ ተቋማትን በመዝረፍ ተግባር ላይ መሰማራታቸውም ተሰምቷል፡፡ ይህን ተከትሎም የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት ካይስ ሰይድ ባስተላለፉት መልእክት ችገራችሁ የገባኛል ግን ደግሞ እስካሁን የኖርንው በሞራል ልእልና እንጂ በስርቆትና በዝርፊያ አይደለም ብለዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ሰልፉን ለመበተን ከተሰማሩ የፀጥታ ሃይሎ ጋር ግጭት ውስጥ የገቡ ሲሆን ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት አድርገዋል፡፡

የተቃውሞውን ግርግር ተከትሎ በግል ንብረቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ዘረፋና ውድመት ለመከላከል የሀገሪቱ ጦር ሃይል በርካታ ወታደሮችን በተለያዩ አካባቢዎች አሰማርቷል ተብሏል፡፡ ባለፈው እሁድ ብቻ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡት ሰዎች መካከል ከ160 በላይ የሚሆኑት በፀጥታ አስከባሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰምቷል፡፡ ሰልፈኞቹ ከሚያነሷቸው ጥያቄዎች መካከል የሀገቱ ምክር ቤት ይበተን የሚለው ይገኝበታል ነው የተባለው፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply