ትራምፕ በግድቡ ዙሪያ የሰጡትን አስተያየት በመቃወም ሩሲያ እና መሰል የላይኛው ተፋሰስ አባል ሀገራት የጠራ አቋም እንዲይዙ እየተሰራ ነው

ትራምፕ በግድቡ ዙሪያ የሰጡትን አስተያየት በመቃወም ሩሲያ እና መሰል የላይኛው ተፋሰስ አባል ሀገራት የጠራ አቋም እንዲይዙ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ዶናልድ ትራምፕ የሰጡትን አስተያየትን በመቃወም ሩሲያ እና መሰል የላይኛው ተፋሰስ አባል ሀገራት የጠራ አቋም እንዲይዙ እየተሰራ መሆኑን በሩሲያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ ተናገሩ።
አምባሳደሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግድቡ ዙሪያ የሰጡት አስተያየት ከእውነታው የተቃረነ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ የጀመረችው ግብፅ በችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት ነው ያሉት መረጃ የተዛነፈ መሆኑን ጠቅሰው፥ ትራምፕ ግድቡ ጠብታ ውሃን ለግብፆች ይነፍጋል ያሉትም ከእውነታው ያፈነገጠ በካይሮ ሰዎች የሀሰት መረጃ የታጀለ መሆኑን ገልፀዋል።
ኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት እየተገነባ ያለው ግድብ የውሃ ፍሰትን ሙሉ በሙሉ እንደማያግድ የተናገሩት አምባሳደሩ የዓለም አቀፍ ልምዶችም ከዚህ እውነታ ያፈነገጡ አይደሉም ብለዋል፡፡
በዚህም ይህን የትራምፕ የተሳሳተ አስተያየት በመቃወም እንደ ኢትዮጵያ የላይኛው ተፋሰስ አባል ሀገራት ለሆኑት ሩሲያ እና ቻይና ጭምር እያስረዳን ሲሉ ተናግረዋል።
እነዚህ ሀገራት የግድብ ፖለቲካን በሚገባ የተረዱ በመሆናቸው በትራምፕ አሳሳች አስተያየት የሚሳሳቱ እንዳልሆኑም ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ ባለፈም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ስለ ግድቡ ትክክለኛ ገፅታ እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
በጀርመኑ የተሽከርካሪዎች ማምረቻ ኩባንያ በፕሮጀክት ባለሙያነት እያገለገሉ የሚገኙት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ በበኩላቸው፥ የትራምፕ አስተያየት በአፍሪካ ላይ ጭምር የተሰነዘረ ነው ብለውታል፡፡
ኢትዮጵያውያን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ዛሬ ላይ የሚይዙት አቋም የቀጣዩ ትውልድን ህይወት የሚወስን መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የትራምፕን አፍራሽ አካሄድ በመቃወም ጀርመን እና ሌሎች የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የኢትዮጵያን በተፈጥሮ ሀብቷ የመልማት መብት እንዲደግፉ እየተሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡

The post ትራምፕ በግድቡ ዙሪያ የሰጡትን አስተያየት በመቃወም ሩሲያ እና መሰል የላይኛው ተፋሰስ አባል ሀገራት የጠራ አቋም እንዲይዙ እየተሰራ ነው appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply