You are currently viewing ትውልዱ ሀይማኖቱን በአግባቡ እንዲረዳ ሻደይ አሸንድየ በዓል የራሱን አስተዋጾ ሲያበረክት ቆይቷል! ከነሀሴ 16 እስከ ነሀሴ 21 ለሚከበረው አሸንዳ አሸንድየ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳቸሁ:…

ትውልዱ ሀይማኖቱን በአግባቡ እንዲረዳ ሻደይ አሸንድየ በዓል የራሱን አስተዋጾ ሲያበረክት ቆይቷል! ከነሀሴ 16 እስከ ነሀሴ 21 ለሚከበረው አሸንዳ አሸንድየ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳቸሁ:…

ትውልዱ ሀይማኖቱን በአግባቡ እንዲረዳ ሻደይ አሸንድየ በዓል የራሱን አስተዋጾ ሲያበረክት ቆይቷል! ከነሀሴ 16 እስከ ነሀሴ 21 ለሚከበረው አሸንዳ አሸንድየ በዓል እንኳን በሰላም አደረሳቸሁ:: (አሻራ ሚዲያ ነሀሴ 14/2014 ዓ.ም) አሸንዳ /አሸንድየ/ በአርተኛው ክፍለዘመን የአገው ህዝቦች ስልጣኔ በሆነው በአክሱም እንደተጀመረ በታሪክ ይነገርለታል። በዓሉ በአማራና ትግራይ ልጃገረዶች የሚከበር በዓል ነው::… አሸንድየ፣ ሻደይ ወይም ሶለል ከነሐሴ 16 እስከ ነሐሴ 21 ቀን ድረስ በአማራና በመላው ትግራይ መከበሩን ሲቀጥል በአሉ በቅርብ ጊዜያት ተወዳጅነቱ በመጨመሩ በደቡብ ኤርትራ፣ በሰሜን ጎንደር፣ እና ሌሎች አካባቢዎችም የሚከበር ባህላዊ እንዲሁም ሀይማኖታዊ ትርጓሜ ያለዉ በዓል ሁኖ ቀጥሏል:: ነሀሴ 16 የሚከበረውን የእመቤታችን የድንግል ማርያም በዓል ምክንያት በማድረግ የሚከበረው ሻደይ አሸንድየ በዓል በትግራይ አሸንዳ, በሰቆጣ ሻደይ,(በኽምጣኛ ቋንቋ ለምለም ማለት) ሲሆን በቆቦ ሶለል በአክሱም አካባቢ ደግሞ ዓይኒ ዋሪ በመባል ይጠራል:: ውብ ጸጉራቸው በሹርባ ተውቧል,መላ አካላቸው በሰፊው የጥጥ ውጤት በሆነው ጸሀይን ያክል በሚያበራ ነጭ ቀሚስ ተሞሽሯል, የክረምቱን፡መልካምነት የዝናቡን ስርዓት የማሳውን ውበት የሚገልጸው አረንጓዴው አሸዳ ቅጠል በልጃገረዶቹ ወገብ ከላይ ወደ ታች ከቀኝ ወደ ግራ ሲዘዋወር ሴትነት ክብሬ ሴትነቴ ማረጌ ያስብላል:: በልጃ ገረዶቹ ጀርባ ላይ የሚታየው አረንጓዴ ሳር በአካባቢው አሸንዳ ቅጠል በመባል ይጠራል:: ይህም ሳር ክረምቱ ሲመቸው በተፈጥሮ የሚበቅልና ልጃገረዶቹ ለበአሉ መዋቢያነት የሚጠቀሙበት ነው:: አሸንዳ አሸንድየ በሴት ልጃገረዶች ተውቦ ሲከበር በአሉን ለማድመቅ አረንጓዴ ቀለም ያለውን ቁምጣ/ቡታንታ/ ከላይ በተመሳሳይ ሰደርያ አጅበው ልብሱን በነጫጭ ቁልፎች አስጊጠው በአሉን በመታደም ጨዋታውን በማድመቅ ከሚያማምሩት ከተዋቡት ልጃገረዶች መካከል የመሰለቻቸውን መርጠው ትዳር የሚመሰርቱ ወንዶችም አይጠፉም:: አሸንዳ የዜማ እና የውበት በዓል ነው፡፡ ሴቶች ለጨዋታው የሚያስፈልጉ አልባሳትና ጌጣጌጥ የማሟላት ቅድመ ዝግጅት ለበዓሉ ሁለት ሳምንት አካባቢ ሲቀረው ጀምሮ ያከናውናሉ፡፡ የአሸንዳ በዓል የፀጉር አሠራሩ ከአልባሶ እስከ ግልብጭ፣ ከጋመ እስከ ድርብ፣ ከደቃቅ እስከ ጉልህ ከሕፃን እስከ አዋቂ ተቆናጅተው ከቱባው ባህል ልብስ አንሥቶ ከዘመናዊው ስፌት ከተገኙት ጃርሲ፣ ሽፎን ቀሚስ ጋር ተኩለው ተውበው የሚታዩበትም ትልቅ ባዓል ነው፡፡ጌጣጌጡም ልዩ ነው አንገት ላይ ከሚንጠለጠለው ሕንቆ፣ እግር ላይ እስከሚጠለቀው አልቦ ያካትታል ጫማም በዋናነት ኮንጎ ይጫማሉ ታድያ ይህን የታዘቡ አባቶቻችን የአሸንዳ ልጅ አይተህ አትታጭ እስከማለት ደርሰዋል፡፡ አባባሉም በአሸንድየ ሶለል በዓል ዕለት ሁሉም፡ልጃ ገረዶች ውብ ይሆኑና ለመምረጥ ትቸገራለህ ሲሉ ነው:: አሸንድየ ልጃገረዶች በየሰፈራቸው በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ቤት ለቤት እየዞሩ በጭፈራ በዘፈን በውዳሴ ሰውን እያወደሱ በተወሰኑ ቀናት ገንዘብ ከሰበሰቡ በኋላ ድግስ ደግሰው በድልቂያ በዘፈን ድግሳቸውን የሚበሉበት, የሚቦርቁበት ባህል ነው:: ልጃ ገረዶች ቀን ቀን የተጎነጎንውን አሸንድየ ወገባቸው ላይ አስረው በየ መንደሩ እየዞሩ የሚጨፍሩ ሲሆን ማታ ማት ደግሞ የተጎነጎነውን አሸንድየ ከወገባቸው በመፍታት በሚቀጥለው ቀን ላለው ጭፈራ እንዳይጠወልግ ጤዛ ውስጥ ያሳድሩታል:: አሸንድዮ ባይ ልጃገረዶች ወደሚያወድሱት ቤት ሲገቡ የዘፈኑ መሪ ቆንጆ “እሜቴ አሉ ደና ወይ” ስትል ተቀባዮቹ “አሉ እንጂ ግቢ ይላሉ እንጂ” ብለው በህብረት ያዜማሉ:: ከዚያም አሸንድየ ወየ ይላል እየተባባሉ ዜማው, ዘፈኑ ስጦታውን እስኪቀበሉ ድረስ የተለያዩ የውዳሴ ስንኞች እየተቋጠሩ ይቀጥላሉ:: የአሸንዳ በዓል የበዓሉ ኩነት ለከተማው ወይም ለአካባቢው እንግዳ ሆነ ብቻ ሳይሆን በዚያው ከተማ የሚኖሩትን ጭምር ቀልብ ይገዛል፡፡ በዓሉ በፀጉር አሠራርና በአልባሳት፣ በመዋቢያ ቁሶችና በመጋጋጪያዎች ብቻ አይደለም የሚገለጠው፣ በዓሉን የሚያጎሉ የተለያዩ ዘፈኖች ይገኙበታል፡፡ በዓሉ በሰፊው በሚከበርበት በሆነው በቅዱስ ላሊበላ ገዳም አገልጋይ የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢው ቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ በጎ አድራጎት ማህበር ስራ አስፈጻሚ በወልድያ ዩኒቨርስቲ የቅዱስ ላሊበላ የቱሪዝም እና ቅርስ ክፍል የቅርስ አስተዳደር የ2ኛ ድግሪ ተማሪ የሆኑት ቀሲስ ይኸነው መልኩ አሸንድየ/ አሸንዳ ጨዋታ ልጃገረዶች አሸንድየ/አሸንዳ/ የተባለ ሳር መሰል ቅጠል ከወገባቸው አስረው እያወዛወዙ ራሱን የቻለ ዜማ ያለው ዘፈን በመዝፈን ከነሐሴ 16-21 የሚከናውኑት በዓል የሆነ እና ሀይማኖታዊይ ይዘቱም ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸውልናል፡፡ ይህ በዓል ከእመቤታችን እርገት በኣል ጋር በአንድ የሚከበር ሲሆን ቅጠሉ ወይም ሳሩ በክረምት ብቻ የሚበቅል ነው የሚሉት ቄስ ይሄነው መልኩ ይሄውም ከእመቤታችን ጾመ ፍልሰታ ዘመን ጋር መገጣጠሙ ልጃገረዶቹ እንደጌጥም እንደ ምሳሌም ሊጠቀሙበት ችለዋል ብለዋል፡፡ የአሸንድየ ሐይማኖታዊ ትርጓሜው ባጭሩ ጨዋታውን ሴቶች ብቻ መጫወታቸው በሄዋን የደረሰን ርግማንን የመለሰች ድንግል ማርያም የሴቶች መኩሪያ ናት እና ስድባችንን አራቅሽልን ሲሉ ነው/ በእንተ ሔዋን ተአጽዖ ኆኅተ ገነት ወበእንተ ማርያም ተርኆ ለነ እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም በኀሙስ ውዳሴ ማርያም ቄጤማው/ቅጠሉ/ በወገባቸው ላይ ሆኖ ሲንቀሳቀሱ የክንፍ ቅርጽ ያሳያል እመቤታችን ስታርግ መላእክት ክንፍ ለክንፍ ተያይዘው እየዘመሩ አሳርገዋታል ይህንንም ልጃገረዶቹ በጨዋታቸው ሰአት ወገባቸው ላይ ባለው ቅጠል ያደምቁታል:: ያስታውሱታል:: ይላሉ ቄስ ይኽነው:: ዳዊት በመሰንቆ እዝራ በበገና ሲያመሰግኗት ሳታውቀው አለፈች ያነን መላከ ሞት እንደተባለው ቅጡሉ አሸንዳ ሙሴ ይባላል፡ ሙሴ ተወልዶ በእናቱ ቤት 3 ወር ከቆየ በኋላ ከባህር ዳርቻ ከቀጤማ ላይ ጥለውት የፈርኦን ልጅ /ተርቡት/ አንስታዋለች እና ያን ሙሴ የወደቀበትን ሳር ለማሰብ አሸንዳ ሙሴ ይባላል፡፡ እስራኤላዊያን ከግብጽ ሲወጡ ባህረ ኤርትራን በተዓምራት ሲሻገሩ የሙሴ እህት ማርያም ከበሮ ይዛ አመሰገነች ይላል ዘጸ 15 የአሮን እኅት ነቢይቱ ማሪያምም ከበሮ በእጅዋ ወሰደች፤ ሴቶችም ሁሉ በከበሮና በዘፈን በኋላዋ ወጡ። 21 ፤ ማርያምም እየዘመረች መለሰችላቸው። በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ።ይህን አብነት አድረገው እነዚህ ደናግላንም ከዓለመ ሐጢአት የዳንብሽ እያሉ እመቤታችንን የሚያመሰግኑ ሆነዋል ሲሉ ቀስ ይኽነው ያብራራሉ፡፡ እነዚህ ባህላዊ ጨዋታዎች ሀይማኖታዊ ይዘት እንዲኖራቸው የቀደሙ አባቶች ሀማኖትን ህጻናት እንዲይዙት እና ህይወት አድርገው እንዲያስቀሩት ከሚወዱት ጨዋታ ጋር እያዛመዱ ያስተምሯቸው እንደነበር ቀሲስ ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ጨዋታ ማህበራዊ ፋይዳ እንዳለውም ይገልጻሉ:: ማንነት የእኔ የሚለው የሚኮራበት ባህሉን ትውልዱ ይዞ እንዲዘልቅ ያደርገዋል፡፡መተዋወቅ መግባባት እና መረዳዳት ያጠናክራል: : ትውልዱ ሐይማኖቱን በአግባቡ እንዲረዳ ያደረግዋል:: ምን ይህ ብቻ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም አለው እንጂ ብለዋል ቀሲስ ይኽነው መልኩ: : ለቱሪዝም ካሉን ቋሚ ቅርሶች በተጨማሪ አማራጭ የገቢ ምንጭ ይሆናል የቱሪስቱን የቆይታ ጊዜ ያራዝማል የአገርን ታሪክ ባህል ለማስተዋወቅ እድል ይፈጥራል ለጥናት እና ምርምር መነሻ ሖኖ ያገለግላል፡: በዓሉ በአሳለፍነው አመት በሀገሪቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት በድምቀት ሳይከበር ማለፉ የሚታወስ ነው:: ይህ በዓል እንደከዚህ ቀደሙ ባማረ እና በደመቀ ሁኔታ አይከበር እንጅ የህዝብ ባዓል ስለሆነ መቸም አይቆምም ጦርነት፣ ሰላም እጦት ግን ተጽኖ አያሳድርበትም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የደርግ መንግስት ለቆ የኢህአዴግ ጦር ላሊበላን በተቆጣረ ዘመን ማለትም 1981 ዓ.ም እና 1982 ዓ.ም በዓሉ በልጃገረዶች ይከናወን ነበር እንጅ አልቆመም:: ለምን የህዝብ እንጅ የተወሰነ የፖለቲካ አካል በዓል ስላልሆነ፡፡ ወደፊትም ሳይበረዝ የህዝብ በዓል ሆኖ ሊቀጥል ይገባዋል ባይ ናቸው ቀሲስ ይኽነው መልኩ:: ወደ ካርኒቫል እና የመንግስት በዓልነት ባይሄድ ደስ ይለኛል ምክንያቱም ይህን የማያበረታታ መንግስት ወይም የፖለቲካ እሳቤ በሚፈጠር ጊዜ ሊቆም ስለሚችል ባይሆን የተለመደው የልጃገረዶች በየመንደሩ የሚያደርጉት ጨዋታ ሲያልቅ ማጠቃለያውን መንግስታት፣ የቤተክርስቲያን አባቶች በአንድ መርሃ ግብር በማሰባሰብ መልክት ሊያስተላልፉ ይችላሉ:: ነገር ግን ከመሰረቱ ቀስቃሹ መንግስት ወይም ድርጅት ከሆነ ህዝባዊ በዓልነቱን ያጣና እንዳሳለፍነው ዓይነት አስቸጋሪ ጊዜ ሲከሰት በዓሉን የሚያዳክም ሊሆን ይችላል የሚል እሳቤ እንዳላቸው ቀሲስ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል:: በመንግስት በኩል አሸንድየ ሻደይ በዓል እውቅናው ከፍ ብሎ ከሁለት አመት በፊት በክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር አልፎም በአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ሲከበር በዓሉን በዩኒስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ እንደሚሰራ መገለጹ የሚታወስ ነው:: ሻደይ አሸንድየ በዓል ዘንድሮም በደመቀ ሁኔታ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ማለትም በላሊበላ ሰቆጣ አላማጣ እና ተመሳሳይ አካባቢዎች ለማክበር ሸር ጉድ የሚያስብል ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል:: እራብ, ሰላም እጦት እና የህዝብ ስቃይ ባልተለየው በትግራይ ክልል ህዝብ ዘንድም በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የህዝብ በዓል ከመሆኑ የተነሳ እንደሚከበር ግምታችንን አስቀምጠናል:: ይህ የአንድነት በዓል ለሀገራችን ህዝብ አንድነትን ሰላምን ፍቅርን እንዲያስተሳስርልን መልካም ምኞታችን ነው:: እንኳን ለ2014 ሻደይ አሸንድየ በዓል አደረሳችሁ የአመት ሰው ይበለን ጤና ይጥልን ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply