ትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች ለተፈናቀሉ ተማሪዎች ዲግሪ እንደማይሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ::

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 20 ፣ 2014 ከትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች ለተፈናቀሉ ተማሪዎች ዲግሪ እንደማይሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ:: ከትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ተፈናቅለው በአደራ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተምረው ለተመረቁ ተማሪዎች፣ መደበኛ ዲግሪ ሚኒስቴሩ ለመስጠት እንደሚቸገር ገልጸዋል፡፡ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በትምህርት ሚኒስቴር ዋስትና ገብተው የተመረቁ ከትግራይ ዩኒቨርሲቲዎች የተፈናቀሉ ከ4ሺህ በላይ ተማሪዎች መደበኛ ዲግሪ ስለተከለከልን ሥራ ለመቀጠርና ለመወዳዳር አልቻልንም ሲሉ ለሪፖርተር ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡

የእነዚሁ የተማሪዎች ቅሬታ የቀረበላቸው ትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑእንደተናገሩት፣ ‹‹የተማሪዎቹ ሙሉ መረጃ ሳይገኝ መደበኛ ዲግሪ ለመስጠት እንቸገራለን፡፡ ጦርነቱ ሲቆምና ሰላምና መረጋጋት በሰሜን ኢትዮጵያ በአስተማማኝ ሁኔታ ሲሰፍን ከመጡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ያቆሙበት መረጃ ተሟልቶ ሲቀርብ ዲግሪው ይሰጣቸዋል፡፡ እስከዚያው ግን በተሰጣቸው ውጤታቸውን በሚገልጽ ሰርተፊኬት ሥራ መፈለግ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህን ቢሉም ከትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች በጦርነት ሳቢያ ተፈናቅለው ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለመመረቅ የተገደዱ ተማሪዎች ግን፣ ትምህርት ሚኒስቴር በአንድ ሴሚስተር የውጤት መግለጫ ወረቀት (በግሬድ ሪፖርት) አሰናብቶናል ሲሉ ቅሬታ ያሰማሉ፡፡ ይህ ወረቀት ደግሞ በሥራ ዓለም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠር እንደማያስችላቸው በመጥቀስ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ዘላቂ መፍትሔ እንዲፈልግላቸው እየጠየቁ ነው፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ግን አሁን ካደረኩት የተለየ አማራጭ የለኝም የሚል ምላሽ ነው ሰጥቷል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply