ቻይና ታዳጊዎች በጌሞች ላይ የሚያሳልፉትን ሰዓት ገደበችቻይና ታዳጊዎቿ በሳምንት ውስጥ በበይነ መረብ ጌሞች ላይ ማሳለፍ የሚችሉትን ጊዜ በሦስት ሰዓት ገደበች፡፡ ከአሁን በኋላ የሀገሪቱ ታዳጊ…

ቻይና ታዳጊዎች በጌሞች ላይ የሚያሳልፉትን ሰዓት ገደበች

ቻይና ታዳጊዎቿ በሳምንት ውስጥ በበይነ መረብ ጌሞች ላይ ማሳለፍ የሚችሉትን ጊዜ በሦስት ሰዓት ገደበች፡፡

ከአሁን በኋላ የሀገሪቱ ታዳጊዎች ጌሞችን መጫወት የሚችሉት አርብ እና የእረፍት ቀናት እንዲሁም በህዝባዊ በዓላት ወቅት ከምሽቱ 2 እስከ 3 ሰዓት ብቻ ይሆናል፡፡

ይህም ቀድሞ ወጥቶ ሲሰራበት ከቆየው ህፃናቱ በእያንዳንዱ ቀናት ለአንድ ሰዓት ተኩል እንዲሁም በህዝባዊ በዓላት ወቅት እስከ ሦስት ሰዓት ጌም በመጫወት እንዲያሳልፉ ይፈቅድ ከነበረው ሕግም ጠበቅ ያለ ነው፡፡

አዲሱ ሕግ በቻይና ያሉና በዓለም ዙርያም እውቅናን ያተረፉ አንዳንድ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን መነቅነቅ ጀምሯል፡፡

ለአብነት ውሳኔውን ተከትሎ ዝነኛው የጌም ኩባንያ ቴንሴንት የአክሲዎን ዋጋው በ0.6 በመቶ ሲወርድ የገበያ ዋጋውም ቀድሞ ጣርያ በነካበት ወቅት ከነበረው የ573 ቢሊዮን ዶላር አሁን ላይ ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር አሽቆልቁሏል፡፡

ኔትኢዝ የተሰኘው ሌላኛው ኩባንያም እንዲሁ የአክሲዮን ዋጋው በ9 በመቶ ወርዷል፡፡

ሕጉ ቻይና ከጌም አንስቶ እስከ ክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎቿ ተፅዕኖዋቸው ከሚገባው በላይ እንዳይሆን ለመቆጣጠር በማሰብ እየወሰደች ያለችው የቁጥጥር እርምጃ አካል ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሀገሪቱ ላለፉት ዓመታት ከፍተኛ እድገት ሲያስመዘግቡ የቆዩትን የኤሌክትሮኒክ ንግድ እና በበይነ መረብ ትምህርት ሰጪ ኩባንያዎች ከፍትሀዊ ተወዳዳሪነት ጋር በተያያዘ አደብ ያስገዙልኛል ያለቻቸውን ደንቦች አውጥታ ነበር፡፡

በዚህም በበይነ መረብ አማካኝነት የሚሰጥ የተጨማሪ ሰዓት ወይም ቱቶሪያል ትምህርን በቅርቡ በማገድ በዘርፉ የተሰማሩትን ኩባንያዎችንም መና አስቀቀርታቸዋለች፡፡

ከሳምንታት በፊት ቴንሴንት እድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ጌሙን መጫወት እንዳይችሉና እንዲጫወቱ የሚፈቀደላቸውም በየቀኑ ከ1 ሰዓት በላይ በህዝባዊ በዓል ቀናት ደግሞ ከ2 ሰዓታት በላይ እንዳይጫወቱ መከልከሉን ቴክስፕሎር ዘግቧል፡፡

በዳዊት አስታጥቄ
ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply