ኑሀ የመንገድ ዳር የመኪና ብልሽት እርዳታ ሰጪ የሞባይል መተግበሪያ በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል፡፡
መተግበሪያው መንገድ ላይ ድንገት ብልሽት ያጋጠማቸውን መኪኖች በ30 ደቂቃ ወስጥ ደርሶ ጥገና ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል፡፡
በመተግበሪያው ወይም በስልክ ጥሪ የሚደረግላቸው ጠጋኞች በአዲስ አበባ በ11ዱም ክፍል ከተሞች ተመድበው አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
የኑሀ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ፍፁም ዘካሪያስ እንዳሉት፣ደምበኞች ምዝገባ ካከናወኑበት ሰዓት ጀምሮ በመኪናው ላይ የሚደርስ ድንገተኛ ብልሽት ቢያጋጥም በኑሀ የሞባይል መተግበርያ ወይም በ6516 ሲደወል ሃላፊነቱን ወስዶ ቢበዛ በ30 ደቂቃ ውስጥ በቦታው ደርሶ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።
ኑሀ የሰለጠኑ ባለሙያዎች በአዲስ አበባ በ11 ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ሲሆኑ በኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክሎች ታግዘው መኪናው የተበላሸበት ቦታ ድረስ በመሄድ ሙያዊ እገዛቸውን ያከናውናሉም ተብሏል።
በተጨማሪም የመኪኖቹ ብልሽት ከፍተኛ ሲሆን በኑሀ የመኪና መጫኛ ወደፈለጉበት ቦታ በነፃ የሚያደርሱ ይሆናልም ነው የተባለው።
የአገልግሎቱ ጥቅል ዋጋም በቀን 9 ብር የሚታሰብ ሆኖ በ3 ወር 825 ብር፣ በ6 ወር 1500 ብር፣ በ1 አመት ደግሞ 3 ሺህ ብር መሆኑ ታውቋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ለጊዜው ምዝገባ ያላከናወኑ ሰዎች አገልግሎት ማግኘት እንደማይችሉ የተገለጸም ሲሆን አገልግሎቱን ለመጠቀም ከዛሬ ጀምሮ መመዝገብ እንደሚያስፈልግም ተጠቁማል፡፡
በረድኤት ገበየሁ
መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም