ናይሪጄሪያዊው ወዶ ገብ፤ ናይጄሪያ ከመኖር ዩክሬን ላይ መዋጋት በስንት ጣዕሙ ማለቱ አነጋጋሪ ሆኗል ሩሲያ ባለፈው ወር ዩክሬንን ስትወር ናይጄሪያዊው ኦታህ አብራሀም በጣም ነበር የተናደደው፡፡…

ናይሪጄሪያዊው ወዶ ገብ፤ ናይጄሪያ ከመኖር ዩክሬን ላይ መዋጋት በስንት ጣዕሙ ማለቱ አነጋጋሪ ሆኗል

ሩሲያ ባለፈው ወር ዩክሬንን ስትወር ናይጄሪያዊው ኦታህ አብራሀም በጣም ነበር የተናደደው፡፡

የ 27 አመት ዕድሜ ወጣቱ ኦታህ አብርሀም ከውጊያ ግንባሩ በ 8 ሺህ 7 መቶ ኪ.ሜ ርቀት ላይ በናይጄሪያ መዲና ሌጎስ በአንድ ትንሽ አፓርትመንት ውስጥ ለብቻው ተቀምጦ በጥሞና ካሰበ በኋላ ወሰነ፤ ስልኩንም አነሳና በትዊተር ገፁ ጦርነቱን መቀላቀል እፈልጋለሁ ሲል አሰፈረ፡፡

ከናይጄሪያ፣ከሴኔጋል፣ከደቡብ አፍሪካ፣ከኬንያና ከአልጄሪያ የሆኑ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ከሩሲያ ጋር ለሚደረግ ጦርነት ነፍጥ አንስተው መዋጋት እንደሚፈልጉ ከገለፁ ወጣቶች መካከል ይሄ ናይጄሪያዊ አንዱ ነው፡፡

ከነዚህ ወጣቶች መካከል ከፊሉ በሀገራቸው ያለውን ተስፋ ቢስ እውነታ ለማምለጥ ጦርነቱን እንደ አንድ አማራጭ ለማድረግ ያሰቡ ናቸው፡፡

ጦርነት እንደሆነ እናውቃለን፣ የልጆች ጨዋታ አይደለም የሚለው የፍልስፍና ምሩቁ ኦታህ አብርሀም፤ እዚህ ከመኖር ግን በዩክሬን ወታደር መሆን በጣም የተሻለ ነው ሲል ተናግሯል፡፡

ጦርነቱ ከለቀ በኋላ እዚያው እንድኖር ሊፈቀድልኝ ከመቻሉም በላይ የማይካደውን ጠላት በመዋጋቴ ደግሞ ጀግና እሆናለው ብሏል፡፡

የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ድሚትሮ ኩሌባ እንደገለፁት እስካሁን ከአለም ዙርያ 20 ሺህ ፍቃደኞች ከዩክሬክ ጎን ቆመው ለመዋጋት ተመዝግበዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌኒስኪ፤ ኑ ከዩክሬናውያን ጎን ቆማችሁ ተዋጉ ሲሉ አለም አቀፍ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው በወታደርነት ለመቀጠር እነዚህ ወጣቶች እየተመዘገቡ ያሉት ሲል ቢቢሲ መዝግቧል፡፡

እኔ ምቹ ህይወት በሀገሬ እየኖርኩ ነው ያለሁት፣ በትምህርትና በሌላ መንገዶች አውሮፓ መሄድ እችላለሁ፣ ግን የአንድ ሀገር ፍትህ ማጣት የሁሉም ነውና፤ ዩክሬንን ለማገዝ ነው በፍቃደኝነት ለመዋጋት የተመዘገብነው ያሉ ባይጠፉም፤ ይሄ ጦርነት አፍሪካዊ ወጣቶች ወደ አውሮፓ ለመግባት ምን ያህል ርቀት ሊጓዙ እንደሚችሉ ያሳየ ነው ሲሉ ብዙዎች አስተያየት እየሰጡ ነው፡፡

ቢቢሲ

ሔኖክ አስራት
መጋቢት 08 ቀን 2014 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply