
“አሁን የሆነውና የተደረገው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደም ስር መበጠስ ነው፤ ይህም የተደረገው በስህተት አይደለም በተጠና መልክ ነው”-ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ይህን የተናገሩት ዛሬ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ በተደረገው የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ላይ ነው፡፡ ብፁዕነታቸው አክለውም ቅዱስ ሲኖዶስ ሕገ ወጥ ናቸው ብሎ አዋጅ የአወጀባቸውን ግለሰቦች በተቃራኒው መንግሥት ሕጋዊ ናቸው ብሎ እየጠበቃቸው ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ድርጊቱን አንድም የመንግሥት አካል አልተናገረም፤ በዚህም ማን እንዳደረገው ማወቅ ችለናል፡፡ ይህንንም ሁሉም ኦርቶዶክሳዊ በደንብ ማወቅ አለበት በማለት ተናግረዋል፡፡ ለዚህም እንደመፍትሔ ልናደርገው የሚገባው እያንዳንዱ ኃላፊ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት የደም ማስቆሙን ሥራ መሥራት አለበት፡፡ ችግሩንም በስብሰባ ብቻ የምንመልሰው ሳይሆን በመንፈሳዊ እና በማኅበራዊ ነገር ራሳችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል፡፡ በተጨማሪም የሕይወት መስዋእትነት ድረስ ተከፍሎ ድርጊቱን ማስቆም ይገባል፡፡ የመጣብን ነገር ሕይወትን የሚጠይቅ ስለሆነ በእምነት አባቶቻችን የተቀበሉትን የሰማዕትነት ጽዋ መቀበል ግድ ይለናል፡፡ በመጨረሻም ብፁዕነታቸው እንደገለጹት በጾመ ነነዌ እንደ ነነዌ ሰዎች በመሆን በንስሐ፣ ጥልቅ በሆነ መንፈሳዊነት፣ ከዓለማዊ ፍላጎት ልባችንን በማንጻት፣ በጸሎት የእግዚአብሔር ረዳትነት መጠየቅ ይገባናል፡፡ ይህንንም አድርገን ከሠራን የሠይጣንን አሠራር በእግዚአብሔር ረዳትነት እናሸንፈዋለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት
Source: Link to the Post