አለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው እና በሀገራችን ህገ መንግስት የሰፈሩ መብቶች ሳይሸራረፉ እንዲከበሩ ለማድረግ መንግስት ግዴታውን ለመወጣት ፈቃደኛ አይደለም ተባለ።

ሀገሪቷ የሰላም አየር እንድትተነፍስ መንግስት የህግ የበላይነት በማረጋገጥ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች
ማክበር እንዳለበትም ነው ጎጎት ፓርቲ ያስታወቀው።

ለጉራጌ ህዝብ ነጻነትና ፍትህ እታገላለሁ የሚለው ጎጎት ፓርቲ ወቅታዊና ሃገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል

መንግስት በሀገሪቱ ህገመንግስት የተደነገጉ አለም አቀፍ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ከማድረግ ይልቅ እራሱ መንግስት መብቶቹን እየጣሰ ሰለመሆኑ የወጡ ማስረጃዎች ምሳሌ ናቸው ብሏል ፓርቲው።

በተለይም ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና የመቃወም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ የመደራጀትና ፍትህ የማግኘት ሰብአዊ መብቶች በመንግስት በኩል በግልጽ እየተጣሱ መሆናቸው ፓርቲው ገልጿል።

መንግስት በህግ ማዕቀፍ የሚሰሩ የህጋዊና ተጠያቂ ተቋማት ድምር እንጂ ከህግ በላይ የሆኑ ግለሰቦች እና ቡድኖች መፈንጫ መሆን የለበትም ብሏል።

መንግስት ከስልጣን ጥማት፣ ከአቅም፣ ከቅንነት፣ ከአሰራር እና አደረጃጃት አንፃር ህዝብን ለከፍተኛ ችግር እየዳረጉ ያሉ መንግስታዊ ውስንነቶች በፍጥነት አርሞ ለህዝብ የገባውን ሀገርና ህዝብን የመጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ፓርቲው አሳስቧል።

ተቃዋሚ እና ተፎካካሪ ሃሳቦችንና ቡድኖችን ከመፍራት፣ ከመግፋትና ከመፈረጅ ወጥቶ የሀገር ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ሲባል ቁጭ ብሎ የመነጋገር፣ የመደራደር እና ሰጥቶ የመቀበል ልምምድ መጀመር አለበትም ብሏል።

ሁሌም የጦርነት መቋጫው ድርድር ነው” እንዲሉ ከብዙ ጥፋት በኋላ የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት አንፃራዊ ሰላም እንዳመጣው ሁሉ አሁንም በሌሎች አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች በድርድር ለመቋጨት መንግስት የመሪነቱን ሚና መጫወት ይጠበቅበታል ሲል ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

የሐገሪቱ ህዝብ ዋነኛ ጠላት ድህነትና ኋላ ቀርነት ሆኖ ሳለ ህዝባችን ለበለጠ ድህነትና ኋላቀርነት እየዳረጉ ያሉ ግጭቶች በዘላቂነት እንዲቆሙ የፖለቲካ ምህዳር ማሻሻያ እርምጃዎች መውሰድ ቀዳሚ እርምጃ መሆን እንዳለበትም ፓርቲው አስታውቋል።

ሔኖክ ወ/ገብርኤል

ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply