አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ሸማቹና የንግዱ ህብረተሰብ ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል- የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ሸማቹና የንግዱ ህብረተሰብ ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል- የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ሸማቹና የንግዱ ህብረተሰብ ከመንግስት ጎን ሊቆም እንደሚገባ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ።

የኢፌዴሪ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እየተወሰደ ያለውን የህግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር ተከትሎ በገበያ ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር በየደረጃው ካለው መዋቅር ጋር መሰራት ስለሚገባቸው ስራዎች፣ የአቅርቦት ችግሮች እንዳያጋጥሙ እና ያልተገባ ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩትን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የሚያስችል እቅድ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱ ተጠቁሟል።

ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ በግብይት ምክንያት የወጪ ንግዱ እንዳይቀንስ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፥ በለፉት 4 ወራት ከወጪ ንግዱ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን እንዲሁም በጥቅምት ወር 280 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 258 ሚሊየን የአሜሪካር ዶላር መገኘቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገልጸዋል።

በገበያ ውስጥ የምርት እጥረት እንዳይከሰትም 392 ሚሊየን ሊትር ዘይት ከቀረጥ ነጻ እና  ከ 4 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስኳር ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ለአብነት ያነሱት ሚኒስትሩ፥ የምርት አቅርቦት ችግር እንዳይፈጠርም ከገጠር እስከ ከተማ ትስስር እንዲፈጠር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ወቅቱ የመሕር ወቅት እንደመሆኑ የሰብል ምርት አቅርቦትን የተሻለ ለማድረግ በየደረጃ የሚገኙ የመንግስት መዋቅሮች በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንዲያስተካክሉ እየተሰራ ነውም ብለዋል።

ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረቶችን በመቆጣጠር ረገድም በገበያ ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ ተብለው በሚታሰቡ ምርቶች ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግና የምርት አቅርቦት ላይ አትኩረን እየሰራን ነው ያሉት አቶ መላኩ፥  ያለ አግባብ የዋጋ ጭማሬ በሚያደርጉ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ላይ የበር ለበር ጉብኝት በማድረግ አስፈላጊው እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ህግን የማስከብር ኃላፊነት ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚሰራቸው የህግ ማስከበር ስራዎች በተጓዳኝ ሸማቹ ህብረተሰብ አቅሙ ስላለው ብቻ በርካታ ምርቶችን በመግዛት የሚፈጠር አላስፈላጊ የምርት ክምችትን ማስቀረት እንደሚገባ ገልፀዋል።

እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብም በኮቪድ 19 ወቅት ያሳየውን ይሁንታ በዚህ አስቸጋሪ ወቅትም በመድገም ለሚወዳት አገሩና ህዝቡ መጠነኛ ትርፍ ብቻ በማትረፍ ህብረተሰቡን በቅንነት እንዲያገለግልም ጥሪያቸውን ማስተላለፋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

The post አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ሸማቹና የንግዱ ህብረተሰብ ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል- የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply