አሐዱ ባንክ ሐምሌ 9 ቀን 2014 ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታወቀ

ሐሙስ ሰኔ 30 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ታኅሳስ 30 ቀን 2012 አንድ ብሎ ጀምሮ፣ 10 ሺሕ የሚደርሱ ባለአክስዮኖችን ያሰባሰበውና በ564 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል የተመሠረተው አሐዱ ባንክ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ሐምሌ 9 ቀን 2014 ወደ ሥራ እንደሚገባ አስታወቀ።

ባንኩ ዛሬ ሰኔ 30 ቀን 2014 በማርዮት ሆቴል በሰጠው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት ውስንነት እንዲሁም በአገልግሎት አሰጣጥና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ክፍተት መኖሩን አውስቷል። ከዚህ አንፃርም የተሻለ የባንክ አደረጃጀት ይዞ ወደ ገበያ የሚገባ መሆኑን አስታውቋል።

በባንኮች ካለው አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ውስጥ፤ 50 በመቶ እንዲሁም ለተበዳሪዎች ከተሰራጨ የብድር ክምችት 3/4ኛ የሚሆነው በአዲስ አበባ እና አካባቢው ካለ አስቀማጭና ደንበኛ የሚገኝ እንደሆነ ባንኩ በመግለጫው አንስቷል። አሐዱ ባንክ ይህንን ክፍተት ለመሙላትና በገጠር ላለው ማኅበረሰብም አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚሠራ እንደሆነ ተገልጿል።

ባንኩ በተጨማሪም የብድር አቅርቦት፣ የወኪል ባንክ አገልግሎት፣ የገጠር ባንክ አገልግሎት ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ ከማድረስ ጎን ለጎን ወረቀት አልባ አሠራርን ከማጠናከር አንፃር አዲስና የተሻሉ አካሄዶችን እንደሚያስተዋውቅ በመግለጫው ተጠቅሷል።

አንድ ቅርንጫፍ ለአንድ ልጅ የሚል መርህም እንዳለው በመግለጫው ተነስቷል። የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አንተነህ ሰብስቤ ይህን በሚመለከት ሲያስረዱ፤ ባንኩ ከተለያዩ የሕፃናት ማሳደጊያ ድርጅቶች ጋር እንደሚሠራ ጠቅሰዋል። በዚህም መሠረት አንድ ቅርንጫፍ በተከፈተ ቁጥር ለአንድ ወላጅ አልባ ልጅ ኹሉንም ወጪ በመሸፈን እንደሚያሳድግ ተናግረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፤ ባንኩ ወደሥራ ከሚገባበት ዕለት ዋዜማ ባሉት ቀናት የተለያዩ መሰናዶዎች እንዳሉት አዲስ ማለዳ ሰምታለች። ከዚህም መካከል የደም ልገሳ አንደኛ ሲሆን፤ ለተስፋ የካንሰር ሕሙማን መርጃ፣ ለጌርጌሴኖን የአእምሮ ሕሙማን መርጃ እንዲሁም ለስለእናት የበጎ አድራጎት ድርጅት የተለያዩ ስጦታና ድጋፎችን እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ለቅዱስ ላሊበላ ገዳም እድሳት ሥራም ድጋፍ እንደሚደረግ ተጠቅሷል።

ባንኩ የንግድ ምልክት ወይም ብራንዱን በአዲስ መልክ ያሠራ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለትም ምልክቱን ይፋ አድርጓል።

አሐዱ ባንክ ከምርቃቱ ዕለት ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ድረስ በተከታታይ ቅርጫፎቹን 50 ለማድረስ ማቀዱም ተነግሯል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply