አሚጎስና በላይአብ ሞተር ሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ መኪኖችን በብድር ለመስጠት ስምምነት ፈጸሙ

አሚጎስና በላይአብ ሞተር  ሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ መኪኖችን በብድር ለመስጠት ስምምነት ፈጸሙ

አሚጎስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማህበር፣ ከበላይአብ ሞተር ኃ.የተ.የግ.ማ ጋር በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ መኪኖችን ለአባላት በብድር ለመስጠት የሚያስችል የስራ ስምምነት ዛሬ  ጠዋት ረፋዱ ላይ በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ፈጽመዋል፡፡

አሚጎስ ከበላይ አብ ሞተርስ ጋር  ባደረገው በዚህ  ስምምነት መሰረት፣ መስፈርቱን ለሚያሟሉ የማህበሩ አባላት በሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ መኪኖችን  በብድር ያቀርባል፡፡

በአገራችን የሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች ፍላጎት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መምጣቱ የሚነገር ሲሆን፤ የዜጎችን ኑሮ ባማከለ መልኩ በብድር አማራጭ እየቀረቡ የሚገኙት ሀገር ውስጥ የሚገጣጠሙ መኪኖች የፋብሪካ ዋስትና ያላቸው መሆናቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል ተብሏል፡፡

አሚጎስ  ላለፉት አስራ አንድ አመታት ከ7 ሺ 500 በላይ አባላትን በማቀፍ እንዲሁም ለ4000 ያህል አባላቱ የብድር አገልግሎትን በመስጠት በርካቶች ሥራቸውን እንዲያስፋፉና  የራሳቸውን ሥራ እንዲፈጥሩ ማድረጉ ተገልጿል።

ከአስር ዓመት በፊት በዘጠኝ ሺ ብር ካፒታል የተመሰረተው  የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ  ማህበሩ፤አሁን  ላይ ካፒታሉን ከአንድ ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር በላይ ማድረሱን  ለማወቅ ተችሏል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply