አማራዊ ማንነታቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተፈናቅለው በራያ ቆቦ ወረዳ አቧሬ 07 ቀበሌ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ለችግራቸው ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጠየቁ።…

አማራዊ ማንነታቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተፈናቅለው በራያ ቆቦ ወረዳ አቧሬ 07 ቀበሌ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ለችግራቸው ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈለግላቸው ጠየቁ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 26 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የአማራ ሚዲያ ማዕከል ላለፉት ዓመታት በራያ ቆቦ ወረዳ አቧሬ 07 ቀበሌ ተጠልለው የሚገኙ ከ2 ሺህ በላይ የአማራ ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ ወደ አካባባቢው በማቅናት ተመልክቷል። በቆይታውም በጣም አሳዛኝ የሆነ የኑሮ መጎሳቆልን የተመለከተ ሲሆን ከችግሮች መካከል ከፍተኛ የሆነ የመጠለያ እና የቁሳቁስ ችግር መኖሩን ከምልከታውና ከተፈናቃዮች አንደበት ተረድቷል። ተፈናቃዮች እንደገለፁት አማራ በመሆናቸው ብቻ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ከደቡብ ክልል ሚዛን ቴፒና ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ በ2010 ዓ.ም ተገድለዋል፣ተዘርፈዋል፣ተፈናቅለዋል። ከነሃሴ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ አቧሬ 07 ቀበሌ ተጠልለው ያለ በቂ ድጋፍ በችግር ላይ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት። ከቆቦ ከተማ በቅርብ ርቀት በምትገኘው አቧሬ 07 ቀበሌ በዘለቀ የእርሻ ልማት ድርጅት ግቢ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮቹ ለዘመናት ከነበሩበት ቀያቸው ሲፈናቀሉ የደረሰባቸው በደል ልብ የሚሰብር ነው። ከተፈናቃዮች መካከል አሞማ ያነጋገራቸው አባ ተመስገን ደሳለኝ ይባላሉ፤ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ዳሌሰዲ ወረዳ ነው በመስከረም 2010 ዓ.ም በተደራጁ የኦሮሞ ወጣቶች የተፈናቀሉት። ወ/ሮ ባዩሽ መኮንን ደግሞ ከምዕራብ ወለጋ ከቡኖ በደሌ ወረዳ ተፈናቅለው ላለፉት 3 ዓመታት በችግር ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው መንግስት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተማፅነዋል። ከምስራቅ ወለጋ የተፈናቀሉት ቄስ ሲሳይ በለጠም የችግሩን አሳሳቢነት ተናግረዋል። ደሳለኝ አራጌ ደግሞ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከአሶሳ ከተማ በ2010 ዓ.ም በግፍ የተፈናቀለ ነው። በሰሜን ወሎ ዞን የራያ ቆቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መንገሻ አሸብር በበኩላቸው እንደ ወረዳ ማድረግ የምንችለውን እየደገፍን እንገኛለን ብለዋል። እንደአብነትም በርካታ ተፈናቃዮች ለትውልድ አካባቢያቸው ደብዳቤ በመጻፍ የመኖሪያ መሬትን ጨምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደረጉላቸው ስለመሰራቱ ተናግረዋል። ቀለብን በተመለከተ በመንግስት የድጋፍ አሰራር መሰረት በየወሩ እየተሰጣቸው መሆኑን አነወዳንዴ ከክልል ሲዘገይ ግን እስከ 2 እና 3 ወራት የሚዘልቅበት ሁኔታ እንዳለ ነው አስተዳዳሪው የተናገሩት። ዘላቂ መፍትሄን በተመለከተ ግን የችግሩን አሳሳቢነት ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አሳውቀን በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን ብለዋል። ከተፈናቃዮች ጋር ያደረግነውን ቆይታ በአሚማ የዩቱብ አድራሻ የምናጋራ ይሆናል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply