([email protected])
የማንም ደጋፊም ሆነ ተቃዋሚ አይደለሁም፡፡ የሚሰማኝን ግን እንደ አንድ ዜጋ ባመቸኝ መንገድ እገልጻለሁ፡፡ ይህ ደግሞ በመሠረቱ ማንም የማይሰጠኝ ወይም የማይነገፍገኝ ተፈጥሯዊና ዜግነታዊ መብት ነው፡፡ ይህ መብት ግን በወሮበላ የመንግሥት ሹመኞች ስለሚደፈጠጥ ብዙዎቻችን ዝምታን እንመርጣለን፡፡ ዝም ያለ ሁሉ ደግሞ ምንም የማያውቅና ስሜት-አልባ ነው ማለት አይደለም፡፡
የኢሣት ትንታጎች – ሀብታሙ፣ ካሣሁን፣ ኤርምያስና ኢየሩሣሌም – በዚህች ይህችን ማስታወሻ በጫጫርኩባት የዛሬዋ ምሽት ማለትም በመጋቢት ኪዳነ ምሕረት 2011ዓ.ም ያቀረቡትን የዕለታዊ ዝግጅት በሚገባ ተከታተልኩ፡፡ ኤርምያስ በአማራ አካባቢ እንቅስቃሴዎች ተስፋ የቆረጠ ይመስላል፡፡ ዝግጅታቸው በሁለት አጀንዳዎች ላይ ነበር፡፡ በደሴውና በባህርዳሩ የተቃዋሚ ተቃዋሚዎች ጉዳይና በታምረኛው ጠ/ሚኒስትር የሰሞኑ አስደማሚ የተባለ ግን ያልሰማሁትና ልሰማውም ፍላጎት የሚከዳኝ ንግግር ዙሪያ፡፡ ተወያዮቹ በተለይ ሀብታሙና ኤርምያስ ትግስት አጥተው የመናገር ተራቸው እንኳን እስኪደርስ ይቁነጠነጡ ነበር – የጤና እስከማይመስል ድረስ፡፡ የደሴና የባህርዳር ዐማጥያንን ለመወረፍ ቃላት እንዳጠሯቸው ከፊት ገጽታቸውና ከአኳኋናቸው መረዳት አይከብድም፤ በዚያ መልክ ማንንም ሲወርፉና ሲዝቱበት ተመልክቼ አላውቅም፡፡ ቢጨንቃቸው የቀደመውን አሮጌ ሜንጫ ከዛሬውና ብሶት ከወለደው ክላሽን አሳንሰው በማየት ሜንጫና ገጀራ ይዞ ወደ አደባባይ መውጣት እንዲያውም ተቃውሞን ከመግለጽ አኳያ የተሻሉ አማራጮች እንደሆኑ በኩራት መሰከሩ – ምን ጥልቅ አድርጎኝ የአንድን ሰው የመሞቻ መሣሪያ የመምረጥ መብት እዳፈራለሁ ብዬ እንጂ አንገት የሚበጥስን ሜንጫ ሰውነትን ከሚበሳ ክላሽን ጋር ማወዳደር ያስፈለገበት ምክንያት ፈጽሞ አልገባኝም – የአማራን እንደለመደው ፀጥ ረጭ ብሎ መገዛት አስፈላጊነት ለማጠየቅ ካልሆነ በስተቀር፡፡ ያኔ በስፋት እንደሚነገረው ኢሣትና አንዳንድ የግዘጣ ሙያ ባልደረቦቹ በርግጥም የግንቦት ሰባት አባላት እንደሆኑ ጠረጠርኩ፡፡ ጋዜጠኝነትና የፖለቲካ ድርጅት ሲገጣጠሙ አየሁ፡፡ “ፊስቱላ” ማለት አሁን ነው፡፡
ያስጠረጠረኝ ደግሞ ኤርምያስ ዘመድ የሞተበት ያህል ፊቱን በሀዘን ከስክሶ ባልተለመደ ፍርደገምድላዊ ፍርዱ “የአማራ ክልል መንግሥት ባህርዳር ላይ ለግንቦት ሰባት ስብሰባ መጨናገፍ ይቅርታ መጠየቅና ‹አሸባሪዎቹ›ን (የኔ ቃል ናት) ለፍርድ ማቅረብ አለበት፡፡” ብሎ በልበ ሙሉነት መናገሩ ነው – ብአዴንን መናቅ እንዲህ ነው፤ ኦህዲድን ወይም ኦነግን ወይም ሕወሓትን ቢሆን እንዲህ እንደማይላቸው ሞቶ በሞቶ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለማንኛውም ለርሱ የነበረኝን ፍቅርና አድናቆት ለጊዜው ደበቅ አድርጌ ጀብድ የተሞላበት ደፋርነቱን አደነቅሁለት፡፡ ይህችን “ይቅርታ ጠይቁ” የምትል የወያኔ ዜማ እንዴት አሁን ሊጠቀምባት እንደፈለገም ሌላ ጥርጣሬ ገባኝ፡፡ እርሱም “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” እንዲሉ መጋቢት 17 ቀን 81 ዓ.ም በጥቂት ኦሮምኛ ተናጋሪ ምርኮኛ የደርግ መንግሥት ወታደሮች ሰሜን ሸዋ ደራ ከተማ ላይ በሕወሓት የተጠፈጠፈው ኦህዲድ እንኳን ባቅሙ የሚጫወትበት ብአዴን በፈለግነው መንገድ ብንተቸው ምንም አያመጣም ከሚል ንቀት የመነጨ የሥነ ልቦና መነፋፋት መሆን አለበት፡፡ ግን ያ እነሱ በሚረዱት መልክ የተረዱት ብአዴን እነሱ በተረዱት መልክ የወረደ ቁመና እንዳለውና እንደሌለው እየቆዬን የምናየው ይሆናል፡፡ ይህ የኢሣት ንቀት በራሱ ትልቅ የቁጭት መንስኤ ሆኖት ራሱን ሊለውጥ ይገባል፡፡ “ይቅርታ ይጠይቅ!” ትልቅ መነሳሳት ይመስለኛል – ድፍረት ላለማለት ማሰቤን ተረዱልኝ፡፡
በነገራችን ላይ የኢሣትን ሀገራዊ አስተዋፅዖ በዚህች የተለዬች አጋጣሚ ሳቢያ ማንኳሰስ አልሻም፡፡ ማንም በዚህ ነጥብ ዙሪያ ቢከራከረኝ አንገቴን እሰጣለሁ፡፡ በተለያዬ ግላዊም ይሁን ድርጅታዊ የዓላማና ፍላጎት መለያየት ምክንያት ኢሣትን ጠላነውም ወደድነውም ለሀገራችን ትልቅ መስዋዕትነትን ከፍሏል፤ እየከፈለም ነው፤ ለእምዬ የክፉ ቀን ደራሽዋ አንዱ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው፡፡ ስህተት ሊሠራ ይችላል – ምድራዊ ነውና ፍጹምነትን አንጠብቅም፤ ከጠበቅንም የዋህነት ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ወይ በሌላ አጋጣሚ ቢሳሳት መጠቆምና እንዲያስተካክል ማድረግ እንጂ ፈጽሞውን ማውገዝ ተገቢ አይደለም፡፡ ሚዲያውም(ኢሣትም) በሚደርገው አስተዋፅዖና ሕዝባዊ ፍቅር ሊደሰት እንደሚገባው ባምንም ሊኩራራና በሰይናጣዊ የአይተኬነት ስሜት በዕብሪት ሊኮፈስ እንደማይኖርበት እንደሃሳብ ማንም ቢሰነዝር በበኩሌ አልቃወምም፡፡ አንዱ የሀገራችን ጠላት በውዳሤ ከንቱ መጀነንና ጥሩ ሥራን ማጠልሸት መሆኑን ስለምረዳ ነው እንዲዚህ የምለው፡፡ ምሥጋና አማሳኝ የሚሆንባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉና፡፡…
ራስን ማወቅ አንዳንዴ ጥሩ ነው፡፡ ግንቦት ሰባትን ደግፎ ያን ያህል በአማራ ሕዝብ ላይ መሣለቅ አግባብ አይደለም፡፡ ይህንን ስልም ደሴና ባህርዳር ላይ የተሠራው የተቃዋሚ ተቃዋሚ ተግባር ትክክል ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ዐማጥያኑ ሙሉ በሙሉ ተሳስተዋል፡፡ የ “ጋዜጠኞቹ” አተቻቸት ግን ይህ አማራ-ጠል ድርጅት በሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ የ “አናስገባም ሠርገኛ እደጅ ይተኛ” ዓይነት ጽኑ ተቃውሞ ሲገጥመው ይህን ያህል እሪ አላሉም – ለምን? ምነው ትችታቸውና ውረፋቸው በአማራው ሲሆን እንዲህ ጠነከረ? የአማራው አካባቢ ባጣ ቆይኝ ነው ያላቸው ማን ነው? ምንም እንኳን ግንቦት ሰባት በተለይ በንግግር ደረጃ አማራውን የሚያስከፋ ነገር ባህርዳር ላይ ለጊዜው በከሸፈው ስብሰባ ላይ ይናገራል ብለን ባንጠብቅም እንደአጠቃላይ ግን የአማራው አካባቢ እንደጋለሞታ ቤት ማንም እንደፈለገ ኮተቱን የሚያራግፍበት መግላሊት የሌለው ድስት ሊሆን ይገባዋል ወይ? ይህ የሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ ዓይነት የግንቦት ሰባት አካሄድ እንዴት ሊያዋጣ ይችላል? ጎበዝ ከሆኑ ነቀምትን ማን ያዘባቸው? “ወንድ” ከሆኑ ደምቢዶሎን ማን ያዘባቸው? አማራን ዋስ ጠበቃ የሌለውና ቀን የጣለው ነው ብለው ይሆን? አዎ፣ እውነታቸውን ነው – “የወደቀ ግንድ ምሣር ይበዛበታል”፡፡ ግን ለዕብሪተኛም ዕብሪተኛን ያዝበታልና “አይደፈሬው” ግንቦት ሰባት እነሱው ራሳቸው ጭንቅላቱን ያዞሩት የቀድሞ ታጋያቸው እነሱንም ናላቸውን አዞራቸው – የዘሩት ይበቅላል፡፡ ስብሰባውንና የስብሰባ አዳራሹን የፈቀዱት የክልሉ ባለሥልጣናት ግን እጃቸው ዐመድ አፋሽ ሆነና ይቅርታ እንዲጠይቁ በቀጭን ጌታ አቤቶሁን ኤርምያስ ለገሠ ታዘዙ – ኤርሚን ለመጀመሪያ ጊዜ ታዘብኩትኝ፡፡ የነገ ወያኔ ከዛሬ ኦህዲድና ከትናንት ወያኔ ካልተማረ ፈርዖናዊ አገዛዙ የፀና አይሆንምና የግንቦት ሰባት ካድሬዎች በ“እንዴት”ና “ለምን” ተደፈርን እንዲያ መብከንከናቸው የማይጠበቅ አልነበረም፡፡
በደሴም ሆነ በባህርዳር ወጣቶቹ ያደረጉት ነገር ዘመናዊ አይደለም፡፡ ያደረጉት ከወያኔ የተማሩትን ነው፡፡ የፈጸሙት ከሌሎች ክልሎች ያዩትን ነው፡፡ አዲስ ነገር አልፈለሰፉም፡፡ ስህተትን በስህተት ለመመለስ ያደረጉት አካሄድ ለውግዘትና ለሰላ ትችት እንደዳረጋቸው እረዳለሁ – መተቸታቸውም ትክክል ነው፤ እንደዚህ ዓይነት ነገር መድገም የለባቸውም፤ ችግራቸው ግን መፈታት አለበት፡፡ እንደዚያ ያደረጉት ሌላ አማራጭ በማጣታቸው ሊሆን እንደሚችል ግን እገምታለሁ፡፡ በሌሎች ቦታዎችም ሲደረግ የታዘቡት እንደዚያ በመሆኑ የነሱ ከናዝሬትና ከአዋሣ የተቃዋሚ ተቃዋሚዎች ድርጊት ባልበለጠ ሁኔታ ፀረ አማራ ነው ብለው የፈረጁትን ድርጅት በክልላቸው እንዳይንቀሳቀስ እርምጃ መውሰዳቸው ያን ያህል ብርቅ ሆኖ በኢንተርሃሞይና ቱትሲ የበረሮ ታሪክ መገለጽ አልነበረባቸውም፡፡ እንዲያውም ለማስፈራሪያነትና ለመደራደሪያነትም ጭምር ድርጅቱን ከጠቀሙ በኋላ እንደኪራይ ዕቃ የትም የተጣሉ ዜጎች ስብሰባን በመበተን ብቻ መቆማቸው ያስመሰግናቸዋል፡፡
ግራም ነፈሰ ቀኝ የግንቦት ሰባት ካድሬዎች ትንሽ የተደናገጡና በዚያም ሰበብ ወጥ ወደ መርገጥ የተሸጋገሩ ይመስላል፡፡ ስህተት ነው፡፡ መጀመሪያ ሕዝብን ማፍቀር ይገባል፡፡ ሕዝብን እየናቁ “ለአንቺ ነው ኢትዮጵያ…” ብሎ መዘመር ለትዝብት ይዳርጋል፡፡ እነዚያ ዜጎች እኮ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ የድርጅቱን ኪስ ከሞሉ በኋላ በዜሮ የትም ሊወረወሩ አይገባቸውም፡፡ ድርጅቱን እንዲህና ከዚህም በላይ የምንወቅሰው ብዙ ስህተት ስለሠራና ራሱን ከማየትና ከማስተካከል ይልቅ በትዕቢት እየተወጠረ በ “ምን ታመጣለህ” አስተዋይነትን የተጠየፈ ቤት-አፈራሽ ዕብሪታዊ ድንቁርናው ስለሚኮፈስ ብቻ ነው፡፡ እንጂ የዜግነት ፖለቲካን ማራመዱ ወርቅ ነው፤ የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታውም በዚያ አቋም ውስጥ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን በማስመሰልና አንዱን ነገድ አርቆ ሌላውን በማቅረብ ሳይሆን ለሁሉም እኩል አመለካከት ሲኖር ነው፡፡ በአማራ ላይ እያሾፉ ደግሞ በክልሉ ለማዘዝ መሞከር አያስኬድም፡፡
ለመሆኑ ግንቦት ሰባት ከሥጋው እየጦመ ከመረቁ አውጡልኝን ለምን መረጠ? አማራን እየጠላ በሌሎችና “በሚወዳቸው ክልሎች” የተነፈገውን ዕድል ለምን በሚጠላው ሕዝብ መሀል ሊያገኝ ፈለገ? ምን ዓይነት ዕንቆቅልሽ ነው? ግንቦት ሰባትም ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሆኖ ሞቶ ሌሎችን በዴሞክራሲን ማቀጨጭ ወንጀል ሲከስ ሀፍረት የለውም፡፡ ወግ ነው ሲዳሩ ማልቀስ፡፡ ለመሆኑ እርሱን የሚተቹ አስተያየቶችንና ዘገባዎችን በሚዲያ አውታሮቹ ያወጣል? እርሱ የማይሆነውን ከሌሎች ለምን ይጠብቃል ታዲያ? እንደግንቦት ሰባት ትዕቢተኛና ቂመኛስ ይኖር ይሆን? ወያኔን ለምን እንጠላለን? በሸረኝነቱና በተንኮሉ አይደለምን? ሌሎችን በኢ-ዲሞክራሲያዊነት ከማበሻቀጥ በፊት በሠሩት ስህተት መጸጸትና ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ብዙ ዝግንትል ገመና ይዞ ሌላውን መውቀስ በብርጭቆ ቤት ውስጥ እየኖሩ ድንጋይ ለመወርወር ቅድሚያውን እንደመውሰድ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የኢሣትን ሀገራዊ አስተዋፅዖ በዚህች የተለዬች አጋጣሚ ሳቢያ ማንኳሰስ አልሻም፡፡ ማንም በዚህ ነጥብ ዙሪያ ቢከራከረኝ አንገቴን እሰጣለሁ፡፡ በተለያዬ ግላዊም ይሁን ድርጅታዊ የዓላማና ፍላጎት መለያየት ምክንያት ኢሣትን ጠላነውም ወደድነውም ለሀገራችን ትልቅ መስዋዕትነትን ከፍሏል፤ እየከፈለም ነው፤ ለእምዬ የክፉ ቀን ደራሽዋ አንዱ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው፡፡ ስህተት ሊሠራ ይችላል – ምድራዊ ነውና ፍጹምነትን አንጠብቅም፤ ከጠበቅንም የዋህነት ነው፡፡ ስለዚህ በአንድ ወይ በሌላ አጋጣሚ ቢሳሳት መጠቆምና እንዲያስተካክል ማድረግ እንጂ ፈጽሞውን ማውገዝ ተገቢ አይደለም፡፡ ሚዲያውም(ኢሣትም) በሚደርገው አስተዋፅዖና ሕዝባዊ ፍቅር ሊደሰት እንደሚገባው ባምንም ሊኩራራና ለትዝብት በሚዳርግ የአይተኬነት ስሜት ሊኮፈስ እንደማይኖርበት እንደሃሳብ ማንም ቢሰነዝር በበኩሌ አልቃወምም፡፡ አንዱ የሀገራችን ጠላት በውዳሤ ከንቱ መንጠባረርና ጥሩ ሥራን ማጠልሸት መሆኑን ስለምረዳ ነው እንደዚህ የምለው፡፡ ምሥጋና አማሳኝ የሚሆንባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፡፡
በቀጣዩ ጊዜ ስለግንቦት ሰባት አማራ-ጠልነት ያሉኝን ማስረጃዎች ከሥሩ ጀምሬ እገልጻለሁ፡፡ “stay tuned” ይላሉ የፈረንጅ ጋዜጠኞች – እኔም አልኩት፡፡ [email protected]