አማራ በመስዋዕትነት ያገኘውን ነፃነት በውጪ ኀይሎች ጫና አሳልፎ እንደማይሰጥና ወደ ባርነት እንደማይመለስ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተናገሩ

ዋዜማ ራዲዮ- አማራ በመስዋዕትነት ያገኘውን ነፃነት በውጪ ኀይሎች ጫና አሳልፎ እንደማይሰጥና ወደ ባርነት እንደማይመለስ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ የአድዋ የድል በዓል አከባበር ላይ ለበርካታ ታዳሚዎች በባህር ዳር ባደረጉት ንግግር በማይካድራ ጭፍጨፋ ተካሂዶ፣ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ አስነዋሪ ጥቃት በሕወሓት ተፈፅሞ፣ በምዕራባውያን የአማራ ክልል ወረራ እንደፈፀመ አድርጎ ለማቅረብ መሞከር ፍትሐዊነት የጎደለው ነው ብለዋል።

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያቤት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የአማራ ክልል ልዩ ሀይልና የኤርትራ መንግስት ወታደሮች ከትግራይ ክልል ይውጡ ሲል አሳስቦ ነበር።

” ……ምዕራባውያንን ባገኝዩት አጋጣሚ ሁሉ አንገታችንን ሊያስደፉ ይፈልጋሉ። ሰሞኑን የሆነውም ይኸው ነው። ………ከዚህ በኋል ማንም ሃይል የአማራ ክልልን የአማራ ህዝብን አንገት የማስደፋት ሙከራ ቢያደርግ ራሳችንን ለመከላከል ተመጣጣኝ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

” በወልቃይት ጠገዴ የተደርገው ውጊያ የተቀማነውን ማንነታችንን ለማረጋገጥ እንጂ መሬት ለመውረር አይደለም። እኛ ከዚህ በኋላ ነጻ ወጥተናል። ነጻ የወጣ ድንበር ወደ ባርነት ተመልሶ አይገባም” ሲሉ አክለዋል አቶ አገኘሁ።

እኛ ከትግራይ ህዝብ ጋር ጠብ የለንም ፣ ጉዳያችን በአማራነታችን ሲያሳድደን ከነበረው ሀይል ጋር ነው ያሉት አቶ አገኘሁ ” አንድነታችን ለመሸርሸር የሚታገሉ ሀይሎች እንታገላቸዋለን ፣ አማራም ቢሆን”

ከዚህ በኋላ የውጭ ሃይሎች በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ መግባት ማቆም አለባቸው፣
በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ትክክለኛውን ነገር ለአለም ለማስረዳት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

“ወያኔ የፈፀመውን ግፍ ማጋለጥ መቻል አለባቸው።….. በጊዜያዊ ችግር መንበርከክ የለብንም” በማለት ሀገሪቱ የገጠማት ችግር በዓድዋ ወቅት ከነበረው ፈተና ጋር ይመሳሰላል ብለዋል።

The post አማራ በመስዋዕትነት ያገኘውን ነፃነት በውጪ ኀይሎች ጫና አሳልፎ እንደማይሰጥና ወደ ባርነት እንደማይመለስ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተናገሩ appeared first on Wazemaradio.

Source: Link to the Post

Leave a Reply