አሜሪካ በኢትዮጵያ የሰሞኑ የጋዜጠኞች እና ማሕብረሰብ አንቂዎች የጅምላ እስር እንዳሳሰባት ገለጸች፡፡በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንዳለዉ የጅምላ እስሮቹን በተመለከተ የኢትዮጵያ…

አሜሪካ በኢትዮጵያ የሰሞኑ የጋዜጠኞች እና ማሕብረሰብ አንቂዎች የጅምላ እስር እንዳሳሰባት ገለጸች፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እንዳለዉ የጅምላ እስሮቹን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባቀረበው ምክረ ሃሳብ መሠረት የፌደራል እና የክልል ፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ሕጋዊ አሰራሮችን መከተል አለባቸው ብሏል።

በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና የማህበረሰብ አንቂዎች በጅምላ እየታሰሩ ነው ያለው ኤምባሲው የፌደራል እና የክልል የጸጥታ ሀይሎች ተገቢውን የህግ ሂደት እንዲጠብቁና የህግ የበላይነት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጉዳዩን በተመለከተ የገለጸውን ስጋት እንደሚጋራውም ነው ኤምባሲው ያስታወቀው፡

ኢሰመኮ ግንቦት 14/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ የጋዜጠኞችና ማኅበረሰብ አንቂዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለእስር እየተዳረጉ መሆኑን ኮንኖ ነበር።
በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ያሉት ተጠርጣሪዎች ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከመታሰራቸው ባሻገር የተወሰኑት ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና በቤተሰቦቻቸው ያልተጎበኙ መኖራቸውንም ኢሰመኮ ገልጿል።

“በርካታ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን፣ በቤተሰብ አለመጎብኘታቸውን” እንደተገነዘበ የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ከሰሞኑ የፌዴራል መንግሥት እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች በተቀናጀ መንገድ “የሕግ የበላይነትን ማስከበር” በሚል መውሰድ በጀመሩት እርምጃ ጋዜጠኞች እና የማኅብረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር መዋላቸዉ ተገልጿል፡፡

በአማራ ክልል ብቻ ከ4500 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ባሳለፍነዉ ሰኞ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply