አምስት የውኃ ጉድጓዶች በጎርፍና ደለል በመሞላታቸው ምክንያት ከፍተኛ የውኃ እጥረት መከሰቱን የአዲስ አበባ ውኃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ

ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአቃቂ ከርሰ ምድር የውኃ ፕሮጀክት ውስጥ የሚገኙ አምስት የውኃ ጉድጓዶች በጎርፍና ደለል በመሞላታቸው ምክንያት በከተማዋ ከፍተኛ የውኃ እጥረት መከሰቱን የአዲስ አበባ ውኃ እና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታውቋል።

ባለስልጣኑ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በቀን 20 ሺሕ ሜትር ኪዮብ ውኃ የማምረት አቅም ያላቸው አምስቱ የውኃ ጉድጓዶች ንፋስ ስልክና ቂርቆስ ክፍለከተሞችን ጨምሮ በርካታ የከተማዋን አካባቢዎች የሚሸፍኑ ሲሆን አሁን ሙሉ በሙሉ ማምረት አቁመዋል።

በዘንድሮው የክረምት ወቅት ከመደበኛው በላይ የጎርፍ ፍሰት በመኖሩ ምክንያት የውኃ ጉድጓዶችን ከመሰል ችግሮች ለመጠበቅ በተሰራው የመከላከያ ግንብ መቆጣጠር እንዳልተቻለ ተጠቁሟል።

የውኃ እጥረቱን በጊዜያዊነት ለመቅረፍ በሳምንት ኹለት ወይም ሦስት ቀን ውኃ ያገኙ ከነበሩ አካባቢዎች በመቀነስ እጥረቱ ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች እየተላከ እንደሆነም ተገልጿል።

የተፈጠረው ወቅታዊ ችግር እስኪፈታ ድረስ የከተማዋ ነዋሪዎች በትዕግስት እንዲጠባበቁ ባለስልጣኑ ጥሪ አቅርቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply