በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ባጋጠሙ ችግሮች የተነሣ በተፈጠረው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት የኑሮ ውድነቱ እየጨመረ መምጣቱን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ ከኑሮ ውድነቱ ጋርም የሥራ አጥ መጠኑ ጨምሯል፡፡
ችግሩን በጊዜያዊነትና በዘላቂነት ለመፍታት ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንም ተመልክቷል፡፡ ፈተናውን በብቃት ለመሻገር መንግሥት መራር ውሳኔ ሊወስንባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውንም አረጋግጧል፡፡
ችግሩ በዘላቂነት እስከሚፈታ ድረስ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን የሚያቃልሉ ጊዜያዊ ርምጃዎችን መውሰድ አለበት፡፡ በተለይም በችግሩ ላይ ቤንዚን የሚጨምሩ አካሄዶችን ማረም የሚገባ ነው፡፡ ምርትን በተገቢ መጠን ለማምረትና ወደ ገበያ ለማድረስ የሚታዩ የአመራርና የአሠራር ችግሮች መፈታት አለባቸው፡፡
በየአካባቢው የሚዘረጉ ኬላዎች ከሕግ አግባብ ውጭ የሚያካሂዱት እገዳና ዘረፋ በአመራር ቁርጠኝነትና ሕግን በማስከበር ሊፈታ ይገባዋል፡፡
የሕዝቡን ችግር በማባባስ ኪሳቸውን መሙላት በሚፈልጉ ስግብግቦች ላይ አስተማሪ ርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ያለው ሠንሠለት እንዲራዘም በሚያደርጉ ደላሎችና ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ የሕግ የበላይነት ሊከበር ይገባዋል፡፡
ኢንቨስትመንትን፣ ንግድንና የሥራ ፈጠራን የሚያቀላጥፍ አሠራር መዘርጋት አለብን፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲደናቀፍ በሚያደርጉ አመለካከቶች፣ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ተገቢውን የእርምት ሥራ መሥራት ይገባናል፡፡
ለዚህም መላው የፓርቲያችን አመራርና አባላት፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የፍትሕና የጸጥታ አካላት የሚጠበቅባቸውን በቁርጠኝነት እንዲወጡ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል፡፡
የሥራ አጥነትን ለመቀነስ የተጀመሩ ተነሣሽነቶች በተፋጠነና ትርጉም በሚያመጣ መንገድ እንዲከናወኑ፤ በሥራ ዕድል ፈጠራ ለተሠማሩ አካላትም አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡
አምስተኛው ፈተና ሌብነት ነው፡፡ አራት ኃይሎች የጋራ ግንባር ፈጥረው እየፈጸሙት ያሉት ሌብነት የድህነት ወገባችንን እያደቀቀው መሆኑን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአጽንዖት ተመልክቶታል፡፡
በመንግሥት ውስጥ የሚገኙ ሌቦች፣ በባለሀብቱ አካባቢ ያሉ ሌቦች፣ በብሔር ዙሪያ ያሉ ሌቦችና በሚዲያው አካባቢ ያሉ ሌቦች ለአንድ ዓላማ አራት ሆነው እየሠሩ ሀገር እያጠፉ ነው፡፡
በመንግሥት አካባቢ የሚገኙት ሌቦች መዋቅርና ሥልጣናቸውን ይጠቀማሉ፤ በባለሀብቱ አካባቢ ያሉት ሌቦች ደግሞ ገንዘባቸውን ለበለጠ ስርቆት ይጠቀማሉ፤ በብሔር ዙሪያ ያሉት ደግሞ ለሌብነታቸው የብሔር ሽፋን ይሰጡታል፡፡
በሚዲያ አካባቢ ያሉት ደግሞ የሌቦቹን ገጽታ ይገነባሉ፤ ሌቦቹ ሲያዙም ብሔራቸውን እየጠቀሱ ሕዝብ የተነካ ያስመስላሉ፡፡ ሁሉም ዓይነት ሌቦች ፍትሐዊነትን ያዛባሉ፤ የሕዝብን ደም ይመጣሉ፤ ስርቆታቸው እንዳይደረስበት ግጭትና ዐመጽ ያቀሰቅሳሉ፡፡
መንግሥት ሁሉንም ዓይነት ሌቦች ለማጥፋት የጀመረውን ዘመቻ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ለዚህም የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እጃቸውን አስቀድመው ንጹሕ በማድረግ ትግሉን እንዲመሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ ያቀርባል፡፡
ሕዝባችንም በሌቦች ላይ የተጀመረው ዘመቻ ግቡን እንዲመታ መረጃ በመስጠት፣ የሌቦች ተባባሪ ባለመሆንና ከሌብነት የጸዳ ትውልድ በማነጽ ኢትዮጵያን እንዲታደግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
በአጠቃላይ ሀገራችን በወሳኝ ምእራፍ ላይ መሆኗን የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ገምግሟል፡፡ ከሁለት ዓመቱ የጦርነት ጫና እየተላቀቅን ነው፡፡
በየአካባቢው የሚገኙ ሕገ ወጥ ታጣቂዎችን ሥርዓት ለማስያዝ የሠራነው ሥራ ውጤት እያስገኘ ነው፡፡ በግብርና ምርት የተሻለ ውጤት እያገኘን ነው፡፡
በሥራ ዕድል ፈጠራ የተጀመሩ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ነው፡፡ በዲፕሎማሲው መስክ የነበሩብንን ፈተናዎች እየተሻገርናቸው እንገኛለን፡፡
የምናገኘው ርዳታና ብድር እየጨመረ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሦስት ዋና ዋና ኢኮኖሚዎች አንዱ ሆኗል፡፡ በገበታ ለሀገር የጀመርናቸው ፕሮጀክቶች እየተጠናቀቁ ናቸው፡፡
እነዚህን ተስፋ ሰጪ ጅምሮቻችንን ለማጨናገፍ ከየአቅጣጫው የሚወረወሩ ፈተናዎችን መሻገር አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን እንደ ብረት ማጠንከር ወሳኝ ነው፡፡
ተግባራችንና ንግግራችን የታረመና ሕዝብን ወደ ብልጽግና የሚወስድ መሆኑን በየጊዜው ማረጋገጥ አለብን፡፡ ትኩረታችንን በልማት፣ በሰላምና በደኅንነታችን ላይ ብቻ እናድርግ፡፡
ነጻነታችንን በኃላፊነት ማስተዳደር የግድ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱን የሚያቃልሉ፣ ልማታችንንም የሚያፋጥኑ፣ የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ ርምጃዎችን መውሰድ ለነገ የማይባል የቤት ሥራችን ነው፡፡ ዲፕሎማሲያችንን ማስፋትና ማጽናት ቁልፍ ተግባራችን ነው፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ በታሰበለት ጊዜ፣ ዕቅድና ሁኔታ እንዲካሄድና እንዲሳካ ማድረግ ኢትዮጵያ እንዲሳካላት ማድረግ ነው፡፡
የፕሬስ ነጻነትን በተገቢው ሕግ፣ ልክና መጠን፤ ሀገርና ሕዝብን በሚጠቅም ቅኝት ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይገባል፡፡ የእምነት ተቋማት የሕዝብን ሞራልና ዕሤት በመገንባት፣ በሰላምና በልማት ላይ በመሠማራት፣ ለኢትዮጵያ ብልጽግና የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ ተስፋ ይደረጋል፡፡
በመሆኑም የፓርቲያችን አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያን፡-አራቱን ተገዳዳሪ ፈተናዎቻችንን አሸንፈን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ያላትን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት የጀመርነው ጉዞ እንዲሳካ፣ ዕውቀታችሁን፣ ጉልበታችሁንና ገንዘባችሁን በመሠዋት የትግሉ አካል እንድትሆኑ፣ የብልጽግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥሪ ያቀርባል፡፡
መጋቢት 8 ቀን 2015
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
Source: Link to the Post