You are currently viewing አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በፓርቲ አመራሮች እና አባላት ላይ የሚፈጸሙ “እስሮች እና ማዋከቦች” እንዲቆም ጠየቁ 

አራት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በፓርቲ አመራሮች እና አባላት ላይ የሚፈጸሙ “እስሮች እና ማዋከቦች” እንዲቆም ጠየቁ 

በናሆም አየለ

ሶስት ሀገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አንድ ክልላዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ፤ በሰላማዊ የፓለቲካ አመራሮች እና አባላት ላይ እየደረሰ ነው ያሉትን “እስር፣ ወከባ እና ሸፍጥ” እንዲቆም አሳሰቡ። አሁን በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች “በአስቸኳይ” እንዲፈቱም ጠይቀዋል።    

ዛሬ ማክሰኞ ሚያዚያ 1፤ 2016 በጋራ ባወጡት መግለጫ ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡት፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ እናት ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ናቸው። አራቱ ፓርቲዎች ባወጡት በዚሁ መግለጫቸው፤ መንግስት በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ላይ “ከመርህ፣ ከህግ እና ከአሰራር ያፈናገጠ መስመር ይከተላል” ሲሉ ተችተዋል። 

በዚህም ሳቢያ የፓርቲ አመራሮች እና አባላት፤ ተጠያቂነት በሌለው አኳኋን “ወደማይታወቅ ቦታ ይጋዛሉ”፣ “በየእስር ቤቱም ያለፍትህ ይንገላታሉ” ሲሉ ወንጅለዋል። የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ አመራሮቻቸው “ለሶስት ወራት ከታሰሩ በኋላ” መፈታታቸውንም ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

አራቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች “ኢ-ህገ መንግስታዊ አካሄድ” ሲሉ የጠሩት ድርጊት አሁንም “ተጠናክሮ መቀጠሉን” በዛሬው መግለጫቸው አመልክተዋል። የኢህአፓ ሊቀመንበር አቶ ዝናቡ አበራ እና የመኢአድ የማዕከል አደራጅ የሆኑት አቶ ጫንያለው ዘየደ፤  ከስራ ቦታቸው እና ከመኖሪያ ቤታቸው በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተወስደው በእስር ላይ እንደሚገኙ ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል። 

አቶ ዝናቡ በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር የዋሉት የዛሬ ሁለት ሳምንት መጋቢት 17፤ 2016 እንደነበር የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አብርሃም ሃይማኖት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የኢህአፓ ሊቀመንበር በቁጥጥር ስር በዋሉ ማግስት በአራዳ ክፍለ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው እንደነበርም ገልጸዋል። 

መጋቢት 18፤ 2016 በነበረው የችሎት ውሎ፤ ፖሊስ አቶ ዝናቡን “ፋኖን በመደገፍ” መጠርጠሩን እንዲሁም “በአዲስ አበባ ውስጥ ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት ሞክረዋል” የሚል ውንጀላ እንዳቀረበባቸው ምክትላቸው አስረድተዋል። ጉዳዩን የተመለከተው ችሎት ለፖሊስ የ15 ቀናት የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ፤ ለትላንት ሰኞ መጋቢት 30 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ እንደነበር አመልክተዋል። 

አቶ ዝናቡ በትላንትናው ዕለት ፍርድ ቤት መቅረብ የነበረባቸው ቢሆንም፤ “እንዳይቀርቡ ሳይደረግ ቀርቷል” ሲሉ አራቱ ፓርቲዎች በዛሬው መግለጫቸው ላይ ተችተዋል። ፖሊስ አቶ ዝናቡን ፍርድ ቤት ያላቀረባቸው፤ ጉዳያቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለሚከታተለው “ኮማንድ ፖስት ተሰጥቷል” በሚል ምክንያት መሆኑን የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ይህንን ተከትሎም የኢህአፓ ሊቀመንበር እስካሁን ታስረው ከቆዩበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ከሚገኝበት ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ፤ ትላንት ለሊት ወደ አዋሽ አርባ ተወስደዋል ብለዋል። “መንግስት ሰላም ወዳድ ከሆነ፤ ሰላም የሚፈልግ ከሆነ ያሰራቸውን የፖለቲካ እስረኞች፣ ያሰራቸውን ጋዜጠኞች በአስቸኳይ መፍታት አለበት” ሲሉም አቶ አብርሃም አሳስበዋል።

በአራቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫም ተመሳሳይ አቋም ተስተጋብቷል። “በሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አባላት ላይ የሚደርሰው እስራት እና ወከባ፤ ለፖለቲካ ትግሉም ሆነ ለአገር በአጠቃላይ በቀደሙ ጊዜያት ያመጣው ነገር የለም” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ “ዛሬም ቢሆን ከዚህ የተለየ ውጤት የማያመጣ በመሆኑ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በአስቸኳይ [ይቁም]” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። “የታሰሩት አመራሮችም የሃሰት መረጃ ማቀነባበር ሳያስፈልግ፤ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ስንል አጥብቀን እንጠይቃለን” ሲሉም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Source: Link to the Post

Leave a Reply