አሳዛኝ ዜና! በመተማ ወረዳ ከሽንፋ ወደ ገንዳውሃ በተሽከርካሪ ሲጓዙ የነበሩ አማራዎች ታገቱ፤ በቅማንት ስም ከተደራጁ የሽፍታ ቡድን አባላት በተተኮሰ ጥይት አንድ ተሳፋሪ ሲገደል፣ ሁለተኛው…

አሳዛኝ ዜና! በመተማ ወረዳ ከሽንፋ ወደ ገንዳውሃ በተሽከርካሪ ሲጓዙ የነበሩ አማራዎች ታገቱ፤ በቅማንት ስም ከተደራጁ የሽፍታ ቡድን አባላት በተተኮሰ ጥይት አንድ ተሳፋሪ ሲገደል፣ ሁለተኛው ደግሞ ክፉኛ ቆስሏል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ … ህዳር 22 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ በተለይም የሽንፋ ነዋሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ለከፍተኛ እገታ እና ዝርፊያ እየተዳረጉ መሆናቸውን ለአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ተናግረዋል። ከተሽከርካሪ ላይ የተደራጀ እገታ በአማራዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው በቅማንት ስም በተደራጁ ሽፍቶች መሆኑ ተጠቁሟል። ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲፈጸም የከረመው አማራ ተኮር የእገታ ወንጀል እንዳለ ሆኖ በህዳር ወር ብቻ ሁለት ጊዜ በተሽከርካሪ ላይ በነበሩ 29 ሰዎች ላይ አስከፊ እና ነውረኛ የእገታ ወንጀል ተፈጽሟል። እገታው የተፈጸመውም የቅማንት ማህበረሰብ በብዛት በሚኖርበት አካባቢ መሆኑን የሚጠቅሱት የአሚማ ምንጮች ለምንም ለማንም በዘላቂነት በማይጠቅም የተልዕኮ ስራ ላይ የተሰማሩ አካላትን ድርጊት መጠየፍ ከለላ ልንሰጣቸው አይገባም፤ ይልቁንስ አሳልፈን ለህግ በመስጠት አብሮነታችንን የበለጠ ማጠናከር አለብን ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። የአሚማ የመረጃ ምንጮች እንደሚሉት ህዳር 8/2015 ከሽንፋ ወደ ገንዳውሃ ሲጓዝ ከነበረ ተሽከርካሪ ኩሊት በተባለ አካባቢ 20 አማራዎች ታግተው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በተለይም ደግሞ አንዳንዶች እስከ 300 ሽህ ብር ድረስ ከህዝብ ተለምኖ ተከፍሎላቸው ተለቀዋል። የሚመለከተው የመንግስት አካል ተገቢ ህጋዊ እርምጃ እየወሰደ ባለመሆኑ ህዳር 21/2015 ከጠዋቱ 2 ሰዓት ላይ በተመሳሳይ መልኩ 9 አማራዎችን ከሽንፋ በቅርብ ርቀት ድንጋይ ቤት በተባለ አካባቢ አግተዋል። ነገር ግን በተሽከርካሪው ላይ የተኩስ እሩምታ በመክፈት አንዱን ሲገድሉ ሌላኛው ሁለተኛውን ተሳፋሪ ክፉኛ በማቁሰል 7 የሚሆኑትን ደግሞ አግተው ወደ ጫካ መውሰዳቸው ታውቋል። በተተኮሰበት ጥይት የተገደለውም አቶ ጌታቸው አለሙ የሚባል ሲሆን ዲያቆን ንጉሴ ዘውዱ የተባለ ነዋሪ ደግሞ ክፉኛ ቆስሎ በመተማ ሆስፒታል ገብቶ የህክምና እርዳታ እየተደረገለት መሆኑ ተሰምቷል። ይህ የእገታ ወንጀል በተለይም ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ አማራውን ሆንተብሎ በኢኮኖሚ ለማድቀቅ፣ ከቀዬው ለማስለቀቅ እና አካባቢውን ምድረ በዳ ለማድረግ በተላላኪዎች ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አመላካች ነው ተብሏል። በሽንፋ እና አካባቢው ያሉ የጸጥታ አካላትም ለህዝቡ ሊደርሱ ባለመቻላቸው ለሰፊው የአማራ ህዝብ እና ለሀገራቸው ሲሉ ውድ የህይወት ዋጋ የከፈሉት እንደአብነትም የነጭ ወርቅ የልማት ቀጠናው፣ የጀግኖቹ የእነ መቶ አለቃ ደጀኔ መንግስቱ ቀዬ የጥቂት ሌቦችና ሴረኞች መጫዎቻ እየሆነ ይገኛል ሲሉ ተደምጠዋል። መቀመጫቸውን ከመተማ ገንዳውሃ 54 ኪ/ሜ ርቀት ላይ ያደረጉ የወረዳ አመራሮች በየጊዜው እየመጡ የሽንፋን ህዝብ እያወያዩት እና ችግሩን እየፈቱለት አይደለም ሲሉ ምንጮች አማረዋል። በዚህም የተነሳ ችግሩ በዘላቂነት ይፈታ ዘንድም ሽንፋ ለብዙ ዓመታት እያነሳው ያለው ራሱን የቻለ የወረዳነት፣ በቅርብ የመስተዳደር እና የመልማት የመብት ጥያቄው ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶ ሊመለስለት ይገባል ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። የጸጥታ ስራ የጋራ ጉዳይ በመሆኑ ማህበረሰቡን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለበት ባለው በዚህ አስከፊ የእገታ ወንጀል ዙሪያ ህዝባዊ ምክክር እና ትብብር በማድረግ መፍትሄ ሊፈለግለት ይገባል ሲሉም ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል። ፎቶ_ፋይል

Source: Link to the Post

Leave a Reply