
አስተሪዮን በመርጡለ ማርያም! መርጡለ ማርያም – የማርያም አዳራሽ ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም… አሻራ ሚዲያ ፣ 👉መርጡለ ማርያም በምስራቅ ጎጃም ዞን ከአዲስ አበባ 367 ኪ.ሜ፣ ከባሕር ዳር 181 ኪ.ሜ፣ ከደብረ ማርቆስ 187 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ጥንታዊት ገዳም ናት፡፡ 👉በሦስት የተለያዩ አቅጣጫዎች ማለትም፡- ከአዲስ አበባ በመነሳት በደጀን-ቢቸና መስመር፣ ከጎንደር ወይም ባሕር ዳር በመነሳት በሞጣ-መርጡለ ማርያም እንዲሁም ከወሎ በመነሳት በደሴ- መካነ ሰላም መስመር በማድረግ ወደ ታሪካዊቷ የመርጡለ ማርያም ገዳም መድረስ ይቻላል፡፡ 👉መርጡለ ማርያም ከዓባይ ወንዝ በቅርብ ርቀት በሚገኝ ኮረብታ ላይ የምትገኝ ስትሆን ወይና ደጋ የአየር ንብረት አላት፡፡ 👉መርጡለ ማርያም በተለያየ ጊዜ ሀገረ ማርያም፣ ሀገረ ሰላም፣ ጽርሐ አርያም እየተባለች ስትጠራ ነበር፡፡ በቦታው ክርስትና ከተሰበከ በኋላ ግን መርጡለ ማርያም ተብላለች ትርጉሙም የማርያም አዳራሽ ማለት ነው፡፡ 👉መርጡለ ማርያም በኢትዮጵያ መስዋዕተ ኦሪት ሲሰዋባቸው ከነበሩት አራቱ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም አክሱም ጽዮን፣ ተድባበ ማርያም፣ መርጡለ ማርያም እና ጣና ቂርቆስ መካከል አንዷ ናት፡፡ በወቅቱ ርዕሰ ርዑሳን በሚል የክብር ማዕረግ ትጠራ ነበር፡፡ 👉በዚህም በሙሴ ዘመን እንደመጡ የሚነገርላቸው እና በኦሪት ዘመን የነበሩ ባለ ስድስት ማዕዘን ድንጋዮችም በአምባው ተተክለው ይገኛሉ፡፡ 👉በመርጡለ ማርያም ክርስትናን እንደተቀበለች በ333 ዓ/ም አካባቢ በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግስት እንደተሰራ የሚታመን በልዩ ልዩ ጌጣ ጌጦች በተዋቡ ድንጋዮች የተሰራ የህንጻ ፍርስራሽ ይገኛል፡፡ 👉 የመርጡለ ማርያም ህንጻ አሰራር እጅግ ረቂቅ የነበረ ሲሆን ዛሬም ድረስ ዓይንን በውበት የሚሞሉ ድንጋይ ላይ የተቀረጹ በአበባና ሐረግ የተጌጠ ሰፊ የበር አምድ፣ መስኮቶች፣ ከህንጻው አናት ላይ የሚገኙ ስዕለ ጽላት፣ ስዕለ ኪሩብ እና ልዩ ልዩ ቅርጻ ቅርጾች ይገኛሉ፡፡ 👉የህንጻው አብዛኛው ክፍል ከውድመት ተርፈው ከነውበታቸው ዛሬም ድረስ ይታያሉ፡፡ አብርሃ ወአጽብሃ የህንጻው አምዶችንና ዓረፍተ መቅደሱ እጅግ በተዋበ የድንጋይ ሐረግ ቅርጽ አስጊጠው በወርቅና በዕንቁ አስለብጠውት እንደነበረም ይነገራል፡፡ 👉ይህ በወርቅ ተጊጦ እንደተሰራ የሚነገርለት አስደናቂ ህንጻ በዮዲት ዘመን በ882 ዓ/ም አካባቢ እንደፈረሰ እና የፈረሰው ህንጻ እንደገና የመታደስ እድል በአጼ በእደ ማርያም ዘመን መንግስት በ1460 ዓ/ም አካባቢ በንግሥት እሌኒ እንዳገኘ ይነገራል፡፡ 👉መርጡለ ማርያም በዋጋ የማይተመን ከፍተኛ የቅርስ ክምችት ያላት ገዳም ናት፡፡ እነዚህ ውድ ቅርሶች በመርጡለ ማርያም ሙዚየም ውስጥ የሚገኙ የአብርሃ ወአጽብሃ የወርቅ መስቀል፣ በ445 ዓ/ም የተጻፈ ግዕዙን በግዕዝ የሚተረጉም አርባዕቱ ወንጌል፣ የአጼ በእደ ማርያም ራስ ቁርና የወርቅ ለምድ፣ የንግሥት እሌኒ የክብር ካባና የብር ዋንጫ፣ የብርና የወርቅ መስቀሎች፣ የወርቅ አክሊሎች፣ የወርቅ ከበሮ፣ የአጼ ገላውዲዮስ ዳዊትና ካባ፣ የኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም (አህመድ ግራኝ) የክብር ካባ፣ የብራና መጻሕፍት እና የመሳሰሉትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ 👉ጥር 21 የሚከበረው በዓለ አስተርዮኦ ማርያም የመርጡለ ማርያም ልዩ የክብረ በዓል ቀን ነው፡፡ አስተርዮኦ ማርያም በመርጡለ ማርያም በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች የሚከበር ደማቅ በዓል ነው፡፡ ዛሬ ከዋዜማው ጀምሮ በሚጀምረው የአስተርዮኦ አከባበር ቅኔና የመርጡለ ማርያም ካህናት የተለየ ጥንታዊ ወረብ ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ክዋኔዎች ይፈፀማሉ፡፡ እንኳን አደረሳችሁ! መረጃው የቪዚት አማራ ነው። “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post