አስተዳደሩ በ2014 በጀት ዓመት 411 ሰዎች በትራፊክ አደጋ መሞታቸውን ገለጸ

1 ሚሊዮን 131 ሺሕ 787 የትራፊክ ደንብ ተላላፊዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል

ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመነት በ2014 በጀት ዓመት 411 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን በዛሬው ዕለት በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

በቁጥጥር ሥራ 8 ዋና ዋና የትራፊክ አደጋ የሚስተዋልባቸው ቦታዎችን ላይ ትኩረት ማድረግ ቢቻልም፤ በበጀት ዓመቱ 411 ሰዎች መሞታቸው እንዳልቀረ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ክበበው ሚገርሳ ተናግረዋል፡፡

ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የዘንደሮው ዓመት አደጋ ጭማሪ ስለማሳየቱም ክበበው አልደበቁም፡፡ በ2013 በጀት ዓመት 389፤ በ2014 ደግሞ 411 ሰዎች በትራፊክ አደጋ በመሞታው የ22 ሰዎች ወይም 6 በመቶ ብልጫ አለው ነው የተባለው፡፡

እንዲሁም በበጀት ዓመቱ 1ሺሕ 900 ሰዎች ላይ ከባድ አደጋ መድረሱንና ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር አደጋው በ76 ሰዎች ወይም 4 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ተብራርቷል። በ2013 1ሺሕ 824 ሰዎች ላይ ከባድ የትራፊክ አደጋ ጉዳት ደርሶ እነደነበርም ክበበው ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም ግን የትራፊክ አደጋ ሞት ቁጥር በመቶ ሺሕ ሕዝብ በ2013 11.6 የነበረ ሲሆን፤ በ2014 ወደ 11.4 ዝቅ ማለቱንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም፤ በሰዓት የተገደቡ የፓርኪንግ ክልከላ ባለባቸው 22 መስመሮች ሕጉን ተላፈው በተገኙ 21 ሺሕ 121፤ ለብዙኅን ትራንስፖርት አግልግሎት የተለዩ መስመሮች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ሕጉን በተላለፉ 8ሺሕ 362፤ ስልክ እያነጋገሩ በሚያሽከረክሩ 6ሺሕ 410 እና ሌሎች ጥሰቶችን በፈጸሙ አሽከርካሪዎች ላይ ርምጃ ተወስዷል ተብሏል፡፡

በተያያዘም ከባድ ጉዳትና የሞት አደጋ ባደረሱ 1ሺሕ 100 (838 ከባድ ጉዳት ያደረሱ እና 262 የሞት አደጋ ላደረሱ) አሽከርካሪዎች መንጃ ፍቃዳቸው እንዲታገድ ለፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን መረጃው ተልኳል፡፡ በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 1 ሚሊዮን 131 ሺሕ 787 የትራፊክ ደንብ ጥሰቶች በሲስተም ማስተናገድ ተችሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ ወደ 5 ሚሊዮን ገደማ ለሚሆኑ መንገድ ተጠቃሚዎች ትምህርት እንደተሰጠም ተመላክቷል፡፡ ለ500 የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ሥልጠና ለመስጠጥ ታቅዶ ለሸገር፤ አንበሳ እንዲሁም ፐብሊክ ሰርቪስ 500 አሽከርካሪዎች እና ለሌሎች አካላት ሥልጠናው እንደተሰጠም ተነግሯል፡፡

The post አስተዳደሩ በ2014 በጀት ዓመት 411 ሰዎች በትራፊክ አደጋ መሞታቸውን ገለጸ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply