You are currently viewing “አስጨነቀኝ ጭንቀታቸው፣  ምንስ ኾኜ ምን ላርጋቸው” መጋቢት 13/2014 ዓ.ም  ጭንቀታቸው ያስጨንቃል፣ ሐዘናቸው ያሳዝናል፣ እናቶች ያነባሉ፣ ልጆች ምግብ ምግብ ይላሉ፡፡ ከጎተራቸው የራቁት…

“አስጨነቀኝ ጭንቀታቸው፣ ምንስ ኾኜ ምን ላርጋቸው” መጋቢት 13/2014 ዓ.ም ጭንቀታቸው ያስጨንቃል፣ ሐዘናቸው ያሳዝናል፣ እናቶች ያነባሉ፣ ልጆች ምግብ ምግብ ይላሉ፡፡ ከጎተራቸው የራቁት…

“አስጨነቀኝ ጭንቀታቸው፣ ምንስ ኾኜ ምን ላርጋቸው” መጋቢት 13/2014 ዓ.ም ጭንቀታቸው ያስጨንቃል፣ ሐዘናቸው ያሳዝናል፣ እናቶች ያነባሉ፣ ልጆች ምግብ ምግብ ይላሉ፡፡ ከጎተራቸው የራቁት፣ ከቀያቸው የተለዩት፣ መሶባቸውን ያጡት እናቶች ከመሶቡ እንጀራ ቆርሰው፣ ከድስቱ ወጥ ጨልፈው፣ ከሌማቱ ቆሎ ዘግነው አይሰጡ ነገር ያ ቀርቷል፡፡ እነርሱም እንደ ልጆቻቸው የሰው እጅ አይተው ነው የሚያድሩት፣ እንጀራ በመሶብ ማስቀመጥ፣ ጎረቤት ለጎረቤት ተጠራርቶ መብላት፣ ቡና እያፈሉ ከጎረቤት ጋር ማውጋት መወያየት፣ ከልጆች ጋር ምክንያት እየፈጠሩ መጫዎትና መደሰት አኹን የለም፡፡ ልጆች በኮልታፋ አንደበታቸው እማማ ምግብ ይላሉ፣ እናቶች አቤት ልጄ እያሉ በእንስፍስፉ አንጀታቸው ያለቅሳሉ፣ እንባቸውን በጉንጫቸው ቦይ ሲያፈሱ ይውላሉ፣ እንቢ አይሉት እርቦታል፣ እንቢ አይሏት እርቧታል፣ እሺ አይሉት፣ እሺ አይሏት ከመሶቡ ምግብ ታጥቷል፡፡ ምጣዱ እንጀራ ርቆታል፡፡ አርሰው እንዳልጎረሱ፣ የተራበን እንዳላጎረሱ፣ ለተቸገረ እንዳልደረሱ ዛሬ የሰው እጅ ያዩ ዘንድ ተገደዱና ልጅና እናት ከቀያቸው ርቀው ሲያልቅሱ ይውላሉ፡፡ በባድማ እየኖሩ፣ ሳይሰለቹ እየሠሩ፣ ልጆች በቀያቸው እየቦረቁ፣ በወገናቸው ደስታ እየሳቁ ሲኖሩ ደስታው ኀያል ነበር፡፡ ልጆች ሲርባቸው፣ እናቶቻቸው ሲያጎርሷቸው፣ አባቶቻቸው ሲያቅፏቸው፣ በልጇ ፈገግታ እናት ስትደሰት፣ በልጆቹ ደስታ አባት ደስታው ከፍ ሲል ማየት ምን አይነት መታደል ኖሯል፡፡ ልጅ ምግብ ስጡኝ እያለ ሲጠይቅ፣ እናት መልስ አጥታ ስትሳቀቅ፣ በችግር ውስጥ ስታለቅስ፣ አንጀቷ ሲላወስ ማየት ሐዘኑ ከባድ ነው፡፡ ልጇ በልቶ የጠገበ የማይመስላት እናት፣ እጅ አጥሯት፣ መላው ጠፍቷት፣ ራበኝ እንኳን ተብላ ተጠይቃ የምታጎርሰው ስታጣ ስብራቷ ከባድ ነው፡፡ እናት ችላ የማትመልሰው መልስ የለኝም ማለትን ነውና ይከብዳታል፣ ያስለቅሳታል፣ ያስጨንቃታል፡፡ እኒያ ሰውን ሳይሰስቱ የሚያፈቅሩ፣ ለሀገርና ለወገን ደስታ የሚኖሩ፣ በእናት ሀገራቸው የማይደራደሩ ደጋግ ሕዝቦች ካላቸው ማጉረስ፣ የራሳቸውን አውልቀው ማልበስ ይችሉበት ነበር፡፡ እኒያ ደግነትንና ጀግንነትን፣ ትዕግስትና አትንኩኝ ባየነትን፣ ብልሃትና ሀገር ወዳድነትን አጣምረው የያዙት የዋግ ሰዎች ኢትዮጵያን የሚዳፈር፣ ወንዙን የሚሻገር በተነሳ ቁጥር ስንቅና ትጥቃቸውን ይዘው እየተነሱ፣ አልመው እየተኮሱ ሀገር አስከብረው ኖረዋል፡፡ ለሚወዷት ሠንደቃቸው፣ ለሚሳሱላት ሀገራቸው፣ ለማትታጠፈው ቃላቸው፣ ለጸናች እምነታቸው ሲሉ በየዘመናቱ አያሌ ታሪኮችን ሠርተዋል፡፡ በታሪክ ድርሳን ውስጥ ከፍ ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ዙፋን እንዲጸና፣ ሀገር አንድ እንድትኾን፣ ወገን እንዲቃና ደማቅ ታሪክ አስፍረዋል፡፡ ታሪክም ከፍ አድርጎ ይዘክራቸዋል፡፡ በመከራ ብዛት እናት ሀገራቸውን አይወቅሷትም፣ በፈተና መበርከት ሠንደቃቸውን አይረሷትም፣ በዘመን መጣመም ቃላቸውን አያጥፏትም፡፡ መከራው ቢበዛ፣ ፈተናው ቢጸና ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር አይቀንስም፡፡ ኢትዮጵያ ለዋጎች ከምንም በላይ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በችግር ጊዜ የሚረሷት፣ በደስታ ጊዜ የሚያነሷት አይደለችም ለዋጎች፡፡ በሚመችም በማይመችም ዘመን የሚጠብቋት፣ የሚሞቱላት፣ በደምና አጥንታቸው የሚያጸኗት ናት እንጂ፡፡ ይሄው ዛሬም እርሷን ባሉ፣ ለኢትዮጵያ በታገሉ ጠላት በዝቶባቸው ከሞቀ ቤታቸው፣ ከሚወዷት ቀያቸው ወጡ፡፡ ማር የሚበሉት፣ በፍየል ቋንጣ የሚቀማጠሉት የሰው እጅ አይተው አደሩ፡፡ የፍየል ወተት የሚጠጡት፣ በበረሃ ወርደው ብርኩታ እየጋገሩ የሚመገቡት፣ ቋንጣ በአገልግላቸው የማይለቁት እኒያ የፍየል እረኞች ዛሬ ላይ ኹሉ ነገር ቀርቶባቸው በመጠለያ ጣብያ ውስጥ ዋሉ፡፡ የብርኩታው መልካም ማዕዛ፣ የፍየሎቹ ጋጋታ፣ ኹሉም ትዝታ ኾኖባቸው ከተወደደች የትውልድ ሥፍራቸው፣ ከሚሳሱላት ቀያቸው ወጥተው የሰው እጅ እያዩ ተቀመጡ፡፡ ብርኩታው፣ ሳቅና ጨዋታው ኹሉም ይናፍቃችዋል፣ ታዲያ ምን ይደረጋል ወራሪ ገፍቷቸው፣ ጀንበር አጋድላባቸው ከሚወዱት ተለዩ፡፡ ሰጥቶ የሰጠ ለማይመስለው፣ አብልቶ ለማይረካው፣ ከሞሰቡ እየቆረሰ ለሚያጎርሰው፣ ከጎተራው እያወጣ ለሚደግሰው ሕዝብ የሰው እጅ አይቶ ማደር ምንኛ ይጨንቃል፡፡ የዋግ ሕዝብ በወራሪዎች ተወርሮ፣ ከቀዬው ተፈናቅሎ በችግር ውስጥ ነው፡፡ ልጆች እየራባቸው፣ እናቶች እየከፋቸው፣ ቀዬና አድባሩ እየናፈቃቸው ነው፡፡ በደል ሳይገኝባቸው፣ ክፋት ሳይኖርባቸው በወራሪዎች ግፍ ቀያቸውን አጥተዋል፡፡ ደስታቸውን ተነጥቀዋል፡፡ አካባቢያቸውን ናፍቀዋል፡፡ የፍቅሯ ከተማ ሰቆጣ ዛሬ ላይ የከፋቸው ልጆች፣ የሚያለቅሱ እናቶች፣ ቀያቸው የናፈቃቸው ንጹሐን ዜጎች መኖሪያ ኾናለች፡፡ “አስጨነቀኝ ጭንቀታቸው፣ ምንስ ኾኜ ምን ላርጋቸው ” እንዳለ ያ የጥበብ ሰው ጥበበኛ ጭንቀታቸው ያስጨንቃል፣ ሐዘናቸው ያሳዝናል፣ ለቅሷቸው ያስለቅሳል፡፡ ምን እንዳርግ ? ብለው ሐሳብ የሚያመነጩ፣ ለተቸገሩት የሚደርስ ንጹሕ ልብ ያለው ያስፈልጋል፡፡ በችግር ውስጥ መኖር ከባድ ነውና ለተቸገሩት መድረስ፣ ለራባቸው ማጉረስ ሰብዓዊ ግዴታ ነውና፡፡ የደረቀውን ጉሮሮአቸውን እናርስላቸው፣ ወዝ ያለው ምግብ ናፍቋቸዋልና እናጉርሳቸው፡፡ “የተገኘውን እንስጣቸው፣ ቸርነቱን አንንሳቸው” እንዳለ ከያኙ ያለንን እንስጣቸው፣ ቸርነቱን አንንፈጋቸው፣ ያዘነውን ልባቸውን እንጠግንላቸው፣ የሚፈስሰውን እንባቸውን እናብስላቸው፡፡ እነርሱ ከኢትዮጵያውን ኹሉ ድጋፍ ይሻሉ፡፡ ወደ ሞቀ ቤታቸው መመለስን ይናፍቃሉ፡፡ በቀያቸው መኖርን ያልማሉ እና፡፡ በጽጽቃ፣ ወለህ እና ሰቆጣ ደስታ የራቃቸው፣ መከራ የጸናባቸው ዜጎች እየኖሩ ነው፡፡ የዝቋላ ወረዳ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ባለሙያ ንጉሡ አዱኛው ዜጎች ባልተመቸ ሁኔታ ውስጥ እየኖሩ ነው ብለውናል፡፡ ችግሩ ጸንቶባቸዋልም ነው ያሉን፡፡ እየተደረገ ያለው ድጋፍም በቂ አለመኾኑን ገልጸውልናል፡፡ ከዚህ ቀደም በምግብ ምክንያት ለሕመም ሲጋለጡ የነበሩ ሕጻናት አሁን ላይ የባሰ ችግር ውስጥ መግባታቸውንም ነግረውናል፡፡ የሕጻናት ጉዳትም ከፍ ያለ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ ኢትዮጵያውያን በችግር ውስጥ ላሉት የዋግኽምራ ነዋሪዎች እንዲደርሱላቸውም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መንግሥትም ሥራውን በትኩረት እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡ “ክው ብሎ ደርቆ አፋቸው፣ የእግዜር ውኃ ሲጠማቸው” እንዳለ ያ ጥበበኛ የእግዚአብሔር ውኃ የጠማቸው፣ የሚጎረስ የራቃቸው፣ ምቹ መኝታ የናፈቃቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ የሚጎርሱት የዕለት ጉርስ፣ የሚለብሱት ልብስ፣ የሚጠጡት ውኃ ይሻሉና ኢትዮጵያውያን ዓይኖቻቸውን ወደዚያ ሥፍራ ያድርጉ፡፡ ደጎቹ ሲቸግራቸው፣ ጀግኖቹ ጀንበር ሲያጋድልባቸው፣ እንግዳ ተቀባዮቹ፣ ባለ አዳራሾቹ ቤት አልባ ሲኾኑ ሐዘኑ ከባድ ነውና ሐዘናቸውን እንጋራቸው፣ ክፉውን ቀን በጋራ መሻገር፣ ሲችግር መተባበር ለኢትዮጵያውያን የተገባ ነውና ትብብር ይሻል፡፡ መተባበር ካለ የከፋቸው ይስቃሉ፣ የተከዙት አንገታቸውን ያቃናሉ፡፡ ምንጭ አሚኮ

Source: Link to the Post

Leave a Reply