አሸባሪውን የሕወሓትን ኃይል ከታሪክ ገጽ ለመደምሰስ ጊዜው አሁን ነዉ -የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 4፣ 2013 ሀገር በመከላከል ዘመቻው ለመሳተፍ እድሜያችሁና ዐቅማችሁ የሚፈቅድላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመከላከያ ሠራዊቱን እንዲቀላቀል ጥሪ ቀረበ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ባደረገዉ ጥሪ ፣ዐቅማችሁ የሚፈቅድላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመከላከያ ሠራዊቱን ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን በመቀላቀል የሀገር ዘብነታችሁን የምታሳዩበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው ብሏል፡፡ አሸባሪውን የሕወሓት ኃይል ከታሪክ ገጽ ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች፣ ይህንን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሣ የክህደት ኃይልና የውጭ እጆች ስውር ደባ ለመደምሰስ ብርቱና የማያዳግም ክንዳችሁን እንድታሳርፉ አቅጣጫ ተቀምጦላችኋል ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫዉ ።

የጸጥታ ኃይሎችን በቀጥታ ለመቀላቀል ያልተቻለው የኅብረተሰብ ክፍል ከመቼውም ጊዜ በላይ ወገቡን አሥሮ በልማት ሥራዎች ላይ ተሳትፎውን ማጠናከር አለበት፤ የመንግሥት ሠራተኛውም በሙሉ ዐቅሙ ያለ ቢሮክራሲ ሥራውን ያከናውን ተብሏል በመግለጫዉ። ሁሉም ዜጋ ነቅቶ አካባቢውን ይጠብቅ፤ የአሸባሪው ቡድን ተላላኪዎች የጥፋት ተልዕኳቸውን እንዳይፈጽሙ ሕዝባችን በዓይነ ቁራኛ ይከታተል፤ ከዚህ ባለፈ ለሠራዊቱ የሚሆን ስንቅ በማዘጋጀትና
የሞራል ድጋፍ በማድረግ ብርቱ ደጀን ይሁን ብሏል መግለጫዉ። ሚኒስቴሩ ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችና ማኅበራዊ አንቂዎች ሕዝቡ ከሀገሩ ጎን እንዲቆም የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታበረክቱ ይጠበቃል። አሸባሪው ሰላማዊ ሰዎች አስመስሎ በየአካባቢው ያሠማራቸው ሰላዮችና የጥፋት ተላላኪዎችን ለመከታተልና ለማጋለጥ እንዲቻል፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ ዐይንና ጆሮ በመሆን ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት ሊሠራ ይገባል ያለዉ መግለጫዉ፤ የሃይማኖት አባቶች በጸሎት፤ የሐገር ሽማግሌዎች በምክር፤ ሁሉም ዜጋ በችሎታው ኢትዮጵያን ብሎ ይቁም ብሏል መግለጫው።

ቀደምቶቻችን እንዲህ ሀገር የሚያጠፋ ጠላት ሲገጥማቸው ስንቃቸውን በአህያ፣ አመላቸውን በጉያ አድርገው ዘምተዋል፤ ሴቶችና ወንዶች፣ ወጣቶችና ጎልማሶች እንደ አንድ ሠራዊት ተምመዋል፤ መሥዋዕትነት ከፍለውም ሀገራቸውን አድነዋል ፤ ዛሬ ያ ታሪካዊ አደራ በእኛ ጫንቃ ላይ ወድቋል ብሏል መግለጫዉ፡፡ የሚኒስቴሩ መግለጫ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ እናት ሀገራችሁ ጥሪ ታቀርብላችኋለች ብሏል። በቃን ብለን ከተነሣን ከፊታችን የሚቆም ምንም ዓይነት ኃይል እንደሌለ ታሪክ ምስክር ነው ያለዉ መግለጫዉ፤ ውጊያው የትግራይን ሕዝብ ምሽግ ካደረገው እኩይ ኃይል ጋር እንጂ ከትግራይ ጋር
አይደለም፤ እናም ስንፋለም መጠቀሚያ የሆነውን የትግራይ ሕዝብ ብሎም መላዋ ኢትዮጵያን ከአሸባሪው ቡድን ነጻ ለማውጣትና የሀገራችንን ሰላምና አንድነት ለማስከበር ነው ብሏል።

ትግላችን አሸባሪው ጀርባ ላይ ተፈናጥጠው ሀገራችንን ለማፈራረስና የኢትዮጵያን ህልውና ለማጨለም ከተነሡ የቅርብና የሩቅ ኃይላትና ሀገራት ጋር ጭምር ነው። ስለዚህ ሁሉም ሀገር ወዳድ ሉአላዊነቱን ለማስጠበቅ በሙሉ ልቡ ይሠለፍ፤ እንደ ጥንቱ ዛሬም የሀገሩን ክብር ላለማስደፈር ቆርጦ ይነሳ። የእውነትም ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች፤ የእኛም ስም በታሪክ መዝገብ በጀግንነት ተመዝግቦ ይኖራል ብሏል መግለጫዉ፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply