“አሸባሪው ህወሓት በለኮሠው እሳት መልሶ እየለበለበው ይገኛል።”፦ የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት

ሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) አሸባሪው ህወሓት በለኮሠው እሳት መልሶ እየለበለበው ይገኛል ሲል የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።

የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ፤ “ሠራዊታችን የድል ሠራዊት ነው!!” ያለ ሲሆን፤ በየትኛውም ቦታና ጊዜ፤ አስቸጋሪ መልክአ ምድርንም ሆነ የአየር ፀባይ ተቋቁሞ ግዳጁን በድል አድራጊነት የሚወጣው የመከላከያ ሠራዊት ጠላትን በአስተማማኝ መመከት የሚችል ኃይል መሆኑን ገልጿል።

“መከላከያ ሠራዊታችን ከራሱ ይልቅ ህዝብን ያስቀደመ፤ ለአገር እና ለህዝብ እራሱን አሳልፎ የሠጠ ብሔራዊ ኩራታችን ነው። ጠላቶቻችን ህዝባዊ ባህሪውን በውል ስለሚገነዘቡ ህፃናትንና ሴቶችን ከፊት አሰልፈው ክፍለ ዘመን ባለፈበት ጦርነት በህዝብ መአበል መዋጋታቸው የሠራዊታችንን አይበገሬነትና ጀግንነት ጠንቅቀው ስለሚያውቁት ነው።” ሲልም ገልጿል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ካለፈው የህልውና ዘመቻዎች የጠላትን አሠላለፍ በውል በመገንዘብ አሸባሪውን የህወሓት ቡድን እንደ አመጣጡ አፀፋዊ ምላሽ እየሠጠው እና እየደመሰሰው እንደሚገኝም በመግለጫው አስታውቋል።

ህወሓት ለዜጎቹ ደንታ እንደሌለው ባሳየው በዚህ የኋላ ቀር ጦርነት ሠራዊታችን በከፍተኛ ጥንቃቄ እና የኃላፊነት መንፈስ ግዳጁን እየተወጣ እንደሚገኝ የገለጸው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት፤ “አሸባሪው ህወሓት በለኮሠው እሳት መልሶ እየለበለበው ይገኛል።” ሲል አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply