አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ አዲስ የአቅርቦትና የሎጅስቲክ አገልግሎት መጀመሩን አስታወቀ

ለአዲሱ ዓመት ዶሮና በግን ጨምሮ የተለያዩ የበዓል ግብአቶችን በአሸዋ የሞባይል መተግበሪያ መገበያየት እንደሚቻልም ተገልጿል

ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ አክሲዮን ማህበር የአለምን ምጣኔ ሀብት እያንቀሳቀሰ በሚገኘው የዲጅታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ በመሰማራት እየሰራ የሚገኝ ተቋም ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት አዲስ የአቅርቦትና የሎጅስቲክ አገልግሎት ይፉ አድርጓል።

ድርጅቱ “በቀልጣፋ፣ አስተማማኝ አቅርቦትና ሎጀስቲክስ ከልዩ ዋስትና ጋር የአገራችንን የግብይት ሥርዓት በአሸዋ ዶት ኮም /Ashewa.com/ እናዘምን!” በሚል መሪ-ቃል በአዲስ አበባ፤ ቀነኒሳ ሆቴል ባከናወነው በዚህ ይፋዊ የአገልግሎቱ ማስጀመሪያና ማስተዋወቂያ መርሃግብር ላይ ከፍተኛ የመንግስት ሀላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተውበታል። በመድረኩ የአሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ አ.ማ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳንኤል በቀለ፤ ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግስት በ2025 ዲጅታል ኢትዮጵያን በመገንባት እየሰራ ያለውን ሥራ በመደገፍ፤ በኢ-ኮሜርስ፣ ኢ-ለርኒንግ እና በሌሎች 11 የቴክኖሎጂ ዘርፎች ውስጥ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የኢ-ኮሜርስ አንዱ አካል በሆነው አሸዋ ዶት ኮም (Ashewa.com) በኩል ደግሞ ይህን ራዕይ ለማሳካት በሙሉ አቅም በሥራ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ የአገራችንን ወግ፣ ባህል እና ሥነ ልቦና መሠረት በማድረግ መሬት ላይ ያለውን ችግር የሚፈቱ፣ የማህበረሰቡን ህይወት የሚያሻሽሉ ብቁ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች ይዞ ወደ ሥራ መግባቱን የገለጹት ዳንኤል፤ በዚህም ምክንያት ድርጅቱን ለማቋቋም ከሚያስፈልገው 200 ሚሊየን ብር ውስጥ 70 ሚሊየኑን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመሸጥ መቻሉን ተናግረዋል።

አሸዋ ዶት ኮም ይዞት የመጣው ሲስተም የኑሮ ውድነትን የሚፈታ፣ የገበያ መረጋጋትን የሚፈጥር እንዲሁም ቀላል እና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ገጠሩን ከከተማው በንግድ ማስተሳሰር የሚያስችል ነው ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ድርጅቱ በአሁኑ ሰዓት ከ1 ሺሕ 500 በላይ ሻጮችን፣ ከ10 ሺሕ በላይ ምርቶችን ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ 5 ሺሕ ምርቶችንም በወር ዉስጥ በማድረስ “በቀልፋ፣ አስተማማኝ አቅርቦትና እና ሎጀስቲክስ ከተሟላ የዌርሀውስ ጋር አጣምሮ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በዛሬው ዕለት በይፉ ሥራ በጀመረው የአቅርቦትና የሎጅስቲክ አገልግሎትም፤ አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀላሉ እና በፍጥነት ለተጠቃሚ እንዲያደርሱ የሚያስችል ሲሆን፤ ድርጅቱ ምርቶቹን በቀጥታ ከዋና አምራቹ መጋዘን ወደ ተጠቃሚዎች፣ ወይንም ወደ አሸዋ ቴክኖሎጂ መጋዘኖች በማድረስ፤ ከዛም ወደተጠቃሚዎች የማድረስን አገልግሎት እንደሚያካትት ተገልጿል።

አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በአዲስአበባ ይጀመራል የተባለ ሲሆን፤ በቀጣይ በኹሉም የኢትዮጽያ ክፍሎች የአቅርቦትና የሎጅስቲክ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል አቅምን በመገንባት ላይ እንደሚገኝም አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ሸማቾች ባሉበት ቦታ ሆነው አሸዋ ዶት ኮም የሞባይል መተገበሪያን በመጠቀም ለበዓል የሚሆኑ ምግብ ነክ የሆኑ ግብአቶችንም ሆነ ዳሮ፣ በግ፣ ፍየል በሬ የመሳሰሉ እንስሳቶች በኦን ላይን መግዛት እንደሚችሉም አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply