አቢሲንያ ባንክ 3ኛውን ዙር ‹‹እችላለሁ›› ፕሮግራም አስጀመረአቢሲንያ ባንክ በየአመቱ የሚከበረውን አለምአቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ለ3ኛ ጊዜ እችላለሁ በሚል መሪ ቃል ባለተሰጥኦ…

አቢሲንያ ባንክ 3ኛውን ዙር ‹‹እችላለሁ›› ፕሮግራም አስጀመረ

አቢሲንያ ባንክ በየአመቱ የሚከበረውን አለምአቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ለ3ኛ ጊዜ እችላለሁ በሚል መሪ ቃል ባለተሰጥኦ ሴቶችን ተሸላሚ የሚያደርግ የውድድር መርሃ ግብር አስጀምሯል፡፡

በሙዚቃው ዘርፍ ተሰጥኦ ያላቸው ተወዳዳሪዎች፤በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሴቶች የሚሳተፉበት ለባንኩ አዳዲስ ደንበኞችን በመመልመል በመለመልዋቸው የደንበኞች ብዛት መጠን ፤በተመረጡ ቲክቶከሮች መካከል ባንኩ ለሴት ደንበኞቹ ያዘጋጃቸውን አደይና ዘሃራ የቁጠባ ሂሳቦችን በተለየ መንገድ የማስተዋወቅ ውድድር፤እንዲሁም የሴት ሥራ ፈጣሪዎችን በአነስተኛ ወለድ ያለማስያዣ ብድር ማመቻቸት የዉድድሩ ይዘት መሆናቸዉ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም የሙዚቃ ተሰጥኦ ያላቸውን ሴት ተሳታፊዎች በማወዳደር በባለሙያና በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰጥ የህዝብ ድምጽ የተለዩ አሸናፊዎችን በየደረጃው ለመሸለም የሚያስችል ዝግጅት ስለማዘጋጀቱ ነዉ የተገለጸዉ፡፡

ተወዳዳሪዎች በሙዚቃው ዘርፍ ተሰጥኦን ያሳያል የሚሉትን ከሶስት (3) ደቂቃ ያልበለጠ የሙዚቃ ሥራ ያለ ሙዚቃ መሣሪያ በቪዲዮ በመስራት በባንኩ ኦፊሻል የማህበራዊ ገፆች ላይ በሚጠቀስ የቴሌግራም አድራሻ መላክ እንደሚኖርባቸዉም ተገልጿል፡፡

ዉድድሩን በአንደኝነት ለሚያጠናቅቁ የ1መቶሺህ ብር፣ ሁለተኛ ለወጡ ደግሞ 75ሺህ ብር እንዲሁም ሶስተኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የ50ሺህ ብር ሽልማት አዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡

ሌላዉ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሴቶች የሚሳተፉበት ዉድድር ደግሞ ለባንኩ አዳዲስ ደንበኞችን በመመልመል በመለመልዋቸው የደንበኞች ብዛት መጠን ተሳታፊዎች የገንዘብ ሽልማት የሚሸለሙበት ነዉ፡፡

በተመረጡ ቲክቶከሮች መካከል ባንኩ ለሴት ደንበኞቹ ያዘጋጃቸውን አደይና ዘሃራ የቁጠባ ሂሳቦችን በተለየ መንገድ የማስተዋወቅ ውድድር ያካሂዳል የተባለ ሲሆን፤በዚህም ውድድር አንደኛ ለሚወጡ ሴቶች የ1መቶሺህ ብር፣ ሁለተኛ ለሚወጡት ደግሞ 75ሺህ ብር እንዲሁም ሶስተኛ ለሚወጡት ደግሞ የ50ሺህ ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል፡፡

የሴት ሥራ ፈጣሪዎችን ለማበረታት በሚል ባንኩ ካሉት 10 ዲስትሪክቶች መካከል ከእያንዳንዱ አምስት የስራ ፈጣሪዎችን በአጠቃላይ 50 የሥራ ፈጣሪ ሴቶችን በመምረጥ በአነስተኛ የወለድ ምጣኔና ካለመያዣ ለእያንዳደቸው እስከ ብር 5መቶ ሺህ በድምሩ 25ሚሊየን ብር የብድር አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታዉቋል፡፡

ባንኩ በስራ ፈጠራ ዉድድሩ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎቱ ያላቸዉ እና መስፈርቶቹን የሚያሟሉ ሴቶች ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 14 ድረስ ባሉት ቀናት በቅርንጫፎቹ በአካል በመቅረብ ጥያቄጣቸዉን በጽሁፍ እንዲያቀርቡ ብሏል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት በሁለት ዙር በተከናወኑ የ‹‹እችላለሁ›› የተሰጥኦና የስራ ፈጣሪ ሴቶች ውድድር በግጥም፤በድምፅና በቲክቶከሮች መካከል በተደረጉ ውድድሮች ብልጫ ያስመዘገቡ ሶስት ሶስት ተወዳዳሪ ሴቶች የገንዘብና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል እንደነበር የሚታወስ ነዉ፡፡

በእስከዳር ግርማ

መጋቢት 02 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply