‘አባባ ጃንሆይ’ የተሰኘ መፅሐፍ ተመረቀ

ቅዳሜ ሐምሌ 2 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በጌታቸው ተድላ (ዶ/ር) የተዘጋጀና የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን የሕይወት ጉዞ የሚተርክ፤ በምስሎች የታጀበ መፅሐፍ ዛሬ ሐምሌ 2 ቀን 2014 በሂልተን ሆቴል ተመርቋል።

በመፅሐፉ ዙሪያ ሐሳባቸውንና ዕይታቸውን ያካፈሉት ዶክተር ወዳጄነህ መኅረነ፤ ለአፄ ኃይለሥላሴ ያላቸውን አክብሮትና አድናቆት በመግለፅ ጀምረዋል። ትህትና፣ ፈርሃ እግዚአብሔር፣ ክብር፣ ጥበብ፣ ታላቅነት፣ ገናናነት እና ግርማዊነት አፄ ኃይለሥላሴን የምገልፅባቸው ቃላት ናቸው ብለዋል። ይህንንም እያንዳንዱን ሰፋ አድርገው ያብራሩ ሲሆን፤ በዛም መካከል በኢትዮጵያ እውነተኛ ብልፅግና የታየበት ዘመን የእርሳቸው ዘመን ነው ብለዋል።

አፄ ኃይለሥላሴ ሰው ሠርቶ፣ ተምሮ፣ ባለሀብት ሆኖ ወይም በሌላ በምንም የማያመጣውና ከላይ ብቻ የሚሰጥ ግርማ ያላቸው ናቸው ያሉት ዶክተር ወዳጄነህ፤ ለእርሳቸው የምንጊዜም ታላቅ የኢትዮጵያ መሪ እንደሆኑም ተናግረዋል።

<<አፄ ኃይለሥላሴን በሚገባው መጠን አላከበርናቸውም። አዲስ አበባ መሃል ላይ ትልቅ ሀውልት እንዲሠራላቸው፣ ታሪካቸውም ለዓለም እንዲነገር እፈልጋለሁ።>> ያሉት ዶክተር ወዳጄነህ፤ የመፅሐፉን አዘጋጅ ደጋግመው አመሥግነዋል።

የመፅሐፉ አዘጋጅ ጌታቸው ተድላ (ዶ/ር)፣ በእለቱ በዝግጅቱ የተገኙትን ጨምሮ መፅሐፉን ለአንባብያን ለማድረስ የረዷቸውን እንዲሁም በተለያየ መንገድ ከጎናቸው የነበሩትን ኹሉ በማመስገን ጀምረዋል።

ይህንን መፅሐፍ ጨምሮ ቀደምት ታሪክ ቀመስ ሥራዎቻቸውን ለማዘጋጀት ምክንያት የሆናቸውን ጉዳይ ሲያነሱ፤ ገጠመኞቻቸውን በማውሳት ትውልዱ የማያውቀውን ለማሳወቅና የተሳሳተውን ለማረም እንደሆነ አስታውቀዋል።

ከ10 በላይ መፅሐፍትን ለአንባብያን ያደረሱት ጌታቸው ተድላ፤ አብዛኛውን የመፅሐፍ ገቢ ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ያበረከቱት ሲሆን፤ አባባ ጃንሆይ የተሰኘው የአዲሱ መፅሐፋቸው ገቢም ለግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ፋውንዴሽን ያበረከቱት ነው።

በዝግጅቱ ላይ ልዑል በዕደማርያም፣ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ አሕመድ ዘካሪያ (ዶክተር) እንዲሁም አርበኞችና የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወዳጆችና ቤተሰቦች ታድመዋል። በመፅሐፍ ምርቃቱ መሰናዶ መጨረሻም ላይ በተለያየ መንገድ አስተዋፅኦ ላደረጉ ኹሉ የምስጋና ሰርተፍኬት ተሰጥቷል።

በዝግጅቱም የተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን፤ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን የሚያወሱና የሚያወድሱ ግጥሞችና ተረኮች የዝግጅቱ አካል ነበሩ። ወርልድ ፋውንዴሽን የሙዚቃ ቡድንም መድረኩን በሙዚቃ አጅቦታል።

በመድረኩም የፊታችን ቅዳሜ ሐምሌ 16 ቀን 2014 በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የአፄ ኃይለሥላሴ 130ኛ ዐመት ልደት እንደሚከበር የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ፋውንዴሽን አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply