
አብንን በተመለከተ…❗️ አብን የአማራ ማሕበራዊ ንቅናቄ እና ብሔርተኝነት የወለደው ነው። የ2008/2009 social movement ብሔርተኛ ድርጅት ሲያዋልድ ግን የአማራ የፓርቲ ፖለቲካ ወይም የብሔራዊ ትግል ቁመና ግምገማ ጥልቀት አለመኖር ጉዞውን ፈትኖታል። ሀ) ከረጅም ጊዜ በኋላ የተፋፋመውን ብሔርተኝነት ገምግሞ እና ወደአንዳች መዳረሻ አላማ ለመውሰድ የሚያስችል <<የፖለቲካዊነት ችግር>> ነው የገጠመው፤ 1ኛ – በአላማ ጥራት፣ በአስተሳሰብ ስትራቴጂ እና ታክቲኮች እንዲሁም በፖለቲካዊ ዘዴዎቹ ላይ የጠራ ነገር ለሕዝቡና ለደጋፊው ማቅረብ እና ማስታጠቅ አልቻለም። 2ተኛ – የአማራ ማሕበራዊ ኃይሎችን ፍላጎቶች በመተንተን ረገድ ከሌሎች ለምሳሌ ከብዐዴን/አዴፓ የተለየ አተያይና ፍላጎት ማቅረብ አልቻለም። የብሔርተኝነት ንቅናቄውን የሚያራምደውን ሕዝብ ፍላጎት ተረድቶ እና ተንትኖ፤ በፖለቲካዊ እሳቤ ወደተፈለገው ግብ አልመራውም። 3ተኛ – አማራውን የማደራጀት ስንፍና ዋጠው። ማንን ለምን እንደሚያደራጅ የማይረዳበት የፖለቲካ ቁመና አራመደ። የማሕበራዊ ንቅናቄ ሙቀቶች ቢወልዱትም ያንን ሙቀት ጠብቆ በአላማና ስትራቴጂ የማደራጀት ሥራ መሥራት አልቻለም። የአማራን ምሁር አላደራጀም፣ የአማራን ወጣትና ነጋዴ አላደራጀም፣ የአማራን አርሶአደርና ዲያስፖራ አላደራጀም ብሎም በየክልሉ ያለውን አማራ ዘነጋውና ተወው። 4ኛ – በውስጣዊ ዲሞክራሲው የወደቀ፣ ከግለሰቦችና ቡድኖች ራስ-ተኮር አሰላለፍና አስተሳሰብ በተጠፈረ ፖለቲካ ተቸገረ። ስለሆነም፦ 1) ቀድሞ ከደጋፊው ብሔርተኛ ኃይል ጋር ተጋጨ። የብሔርተኝነቱን መዳረሻ ለሚጠብቀው ደጋፊ ቀጣይነት ያለው የትግል አጀንዳ መስጠት አልቻለም። ስለሆነም ደጋፊው መንገድ ላይ እንዲቆም የሚያደርግ ፖለቲካ ተከተለና በፓርቲው አመራርና ደጋፊው መካከል ቅራኔዎች ተፈጠሩ። ጭራሹኑ <<ፓርቲ መመስረት መቻላችን ትልቅ ስኬት ነው፣ ከቻላችሁ ሞክሩት>> የሚል እሰጣገባ ይደመጣል። ቀጥሎም ቅራኔዎች ከደጋፊ አልፎ በፓርቲው አመራሮች መካከል ተፈጠሩ፣ በማስከተል በፓርቲው አመራሮችና በፓርቲው መዋቅር መካከል ተዛመቱ። 2) አላማውን ማስፈፀሚያ ስልቶቹና እርምጃዎቹ በአስተሳሰብ ደረጃ እንኳ “ፖለቲካዊ ገቢርነት” ጎደላቸው። ለአብነት የፓርቲው አመራሮች ምክር ቤት መግባት እና ስልጣን መጋራት ለፓርቲው አላማ ምን ማለት ነው!? ከስትራቴጂውና ፕሮግራሙ ጋር ያለው ዝምድና ግልፅ አረዳድ ቢኖር የቅራኔ ምንጭ አይሆንም ነበር። ይባሱንም ጉዳዮቹ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የቅራኔ ምንጭ ሆነ። 3) ከፓርቲው አላማና ግብ ይልቅ በአዴፓ/ብልፅግና ላይ በመጣበቅ፤ የአላማና ቅራኔ ጥገኝነትን ተጋርቶ ቆመ። በብልፅግና ፍላጎቶችና አላማዎች ውስጥ፣ በብልፅግና አሰላለፍ ውስጥ፣ በብልፅግና ቅራኔ ውስጥ አብሮ የሚባዝን (ፓርቲ) አመራር ሆነ። 4) ፓርቲው በአላማው፣ በፕሮግራሙ፣ በስትራቴጂውና ታክቲኩ ሳይሆን በፓርቲው አመራር ግለሰቦች ፍላጎትና ሚና የሚመዘን፣ በግለሰቦች አቋም የሚተችና የሚወደስ ሆነ። የፓርቲው ቁመና የሚተነተው በተነሳበት ፖለቲካ አፈፃፀም ሳይሆን በፓርቲው አመራር ግለሰቦችና ቡድኖች ሚና እና አሰላለፍ ሆነ። ለ) የመዋቅር መዛል ገጠመው። ፓርቲው በስፋት የተዘረጋ መዋቅር አለው። ሆኖም በአስፈፃሚው ቡድን እና በሌላው መዋቅር መካከል ልዩነት አለበት፣ በአስፈፃሚ አመራሮች መካከል ልዩነት አለበት። ፓርቲውን ችግር ውስጥ የከተቱት አንድም በአመራሮቹ መካከል ግላዊና ቡድናዊ የፍላጎት ልዩነቶች አሉ። ሁለትም ከእነዚያ ግላዊና ቡድናዊ ፍላጎቶች የመነጩ የአስተሳሰብና አሰላለፍ ልዩነቶች ተፈጥረዋል። ልዩነቶቹ ከግለሰባዊና ቡድናዊ ፍላጎቶች ውጭ ፖለቲካዊነታቸው ላይ የበለጠ ምርመራ ቢያስፈልግም፤ ▸ የአላማ ልዩነት የሚመስሉ፣ ▸ የስትራቴጂና ስልት ልዩነት የያዙ ፣ ▸ አልፎም የርዕዮተ ዓለም መልክ የተሠጣቸው (በአማራ ብሔርተኝነት እና የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የመዋለል) አስተሳሰቦችና አሰላለፎች ብቅ ብለዋል። ስለሆነም፦ ▸ የጋራ አማራዊ ፍላጎት ማራመድ ተሳነው። ▸ የአማራን አንድነት አደጋ ውስጥ የመክተት አስተሳሰቦች እና ፍላጎቶች ብቅ አሉ። ▸ የወከለው ሕዝብ ጥቃቶችን ትርጉም መስጠት በማይችልበት ደረጃ ቸልተኛ ሆኖ ተቀምጧል። ▸ የደጋፊ አደረጃጀቶች በአገር ውስጥና በውጭ ተለይተውታል። ▸ አሁን ባለበት ቁመና ከ20 አመት በኋላ የመጣው አማራ-ተኮር እና አማራ-ወለድ የፓርቲ ፖለቲካ አደረጃጀት መጥፎ ምልክት የመሆን አማራጭ ዝግ አይደለም። ▲ አሁን ባለበት ቁመናው ግን ብዙ ገዢ መንግስታት የሚጠቀሙት የIncumbent regime “Elite control” እና “Opposition strain” strategies መጠቀሚያ ምሳሌ የሆነ ነው። ከመፍትሔ ጥቆማዎች መካከል፦ 1- የአብንን አስተሳሰባዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በደንብ ተረድቶ መፍትሔ ማስቀመጥ ይገባል። ቀጣይ እርምጃ ከዚህ የሚነሳ ነው። 2- ከውስጣዊ ለውጥ አኳያ የቀረ እድል ካለ አሟጦ መጠቀም። የፓርቲው የለውጥ ኃይል የጀመረው ውስጣዊ የሪፎርም ትግል ወደፊት ተራምዶ የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልተቻለም። ምክንያቱም ብልፅግና እና ምርጫ ቦርድ ባሳዩት የፀረ-ለውጥ ትብብር ፓርቲው በሕገወጥነት በጥቂቶች ፈላጭ ቆራጭነት እንዲቀጥል አድርጎታል። ሕጋዊ ሕልውናው ባበቃበት ጥቂት አፍራሽ አመራሮች እውቅና እያገኙ እንዲቀጥሉ ገዢው ፓርቲ እያደረገ ነው። ስለሆነም በውስጣዊ ለውጥ የመለወጥ እድሉ አነስተኛ ነው። ግን አሁንም በጠቅላላ ጉባኤ አመራሮች የመለወጥና በአዲስ ምዕራፍ የመጓዝ እድሎች ዝግ ናቸው ማለት አይቻልም። ሌሎች አማራጮችም ሊመረመሩ ይችላሉ‼️ ድል ለአማራ‼️ #AmharaStruggle #Justice4Amhara #AmharaGenocide
Source: Link to the Post