አንድ ሲኖዶስ – ሁለት ፓትርያርኮች – ደረሰ ትንቢቱ – ከአዲስ አበባ

ለመታረምና ለመማር በጣም ዝግጁ ነኝ፡፡ በአንድ የንብ ቀፎ ውስጥ ሁለት ንግሥታት ሊኖሩ ይችላሉ ወይ? ሁለት እኩል ሥልጣን ያላቸው ሰዎች አንድ ወንበር ላይ ሊቀመጡ ይቻላቸዋል ወይ? በየአብያተ ክርስቲያን በሚደረጉ ቅዳሤዎችና ጸሎቶች ላይ የሁለት ፓትርያርኮች ስም መነሳቱ አግባብ ነው ወይ? የሁለት ፓትርያርኮች ሹመት ምዕመናኑንና ካህናቱን ውዥምብር ውስጥ አይከትም ወይ? እንዴት ነው ነገሩ! ቃለ ዐዋዲው ተሻሻለ ወይንስ ተጣሰ? ተሻሽሎ ከሆነ መቼና በማን? የሰማሁት ሁሉ እውነት ከሆነ ለነዚህ ጥያቄዎቼ መልስ ባገኝ አልጠላም፡፡ ትልቅ ግርታ ፈጥረውብኛልና፡፡

ማስቀደም የነበረብኝ ነገር ነበር ለካንስ፡፡ እንኳንስ ሁለቱ ሲኖዶሶች ለመታረቅና ሰላም ለመፍጠር በቁ፡፡ ሀገራችን የራቃት ሰላም ይቀርብ ዘንድ ይሄኛውም ድንቅ ጅማሮ ነው – የአካሄድ ችግር ባስተውልበትም፡፡

ይህን የኦርቶዶክሳውያንን ዕርቀ ሰላም በተመለከተ ያልገባኝና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ሰው እንዲያስረዳኝ የምለምነው ነገር አለኝ፡፡ በጥያቄ መልክ ከፍ ሲል ለመጠቆም ሞክሬያለሁ፡፡

ገና ለገና ሁለት ጎራዎችን ለማስደሰት ሲባል ከቀኖና ውጪ የሚደረግ ነገር አንድም ለትዝብት ይዳርጋል፤ አንድም ህገ-ወጥ ለሆኑ የወደፊት አሠራሮች በር ይከፍታል፤ አንድም ከሰማያዊና ከቀኖናዊ ህግጋት ይልቅ የምድራዊ ድርድሮችን ዋጋ ያስበለጠ ያስመስልብንና ከሃቀኛው የነፍስ መንገድ ተንበርካኪውንና መስሎ አዳሪውን የሥጋ መንገድ የመረጥን ለመሆናችን ይህ የዕርቅ ሂደት እንዳያሳብቅብን እፈራለሁ፡፡ በሃይማኖት ውስጥ – እንደሚመስለኝ – በየትኛውም ሁኔታ ከሚገለጥ ሥልጣንና ክብር ይልቅ ለፈጣሪ ህግጋት የሚሰጥ ትኩረት ቅድሚያ ያለው ይመስለኛል፡፡

እንደምድራዊ አካሄድ፣ እንደፖለቲካዊ ችግሮችንና ግጭቶችን የማስወገጃ መንገድ ይህ የተደረሰበት ስምምነት በጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና ሁለት ወገኖችን በአንዴና በእኩል ደረጃ ለማስደሰት ካለን ፍላጎት የተነሣ የእግዚአብሔርንና የቃለ ዐዋዲውን ትዕዛዛት እንዳናፈርስ እሰጋለሁ፡፡ ስሜታዊነት አድሮ ይጠፋል፤ ምክንያታዊነት ግን ዘላለማዊ ነው፡፡ በጠበንጃ እንኳን አይጠፋም፡፡ በውስጥህ ቅሬታ ይዘህ የምትፈጽመው ዕርቅም ሆነ ስምምነት ደግሞ እያደር የሚያመጣው ዳፋ ይኖራል፡፡ አሁንና ዛሬ በሀገር ፍቅር ስሜትም ሆነ በሀገር ናፍቆት ምክንያት ያልታዩን አንዳንድ ነገሮች ነገ ይገለጣሉ፡፡…

በመሠረቱ ድርድር ማለት የማጣት/ የማግኘት ቀመር ነው፡፡ ማጣት ማግኘት ሲባል ደግሞ “ሁሉም እንዳያጣ” ወይም “ሁሉም እንዲያገኝ” ከሚል የቸርነት አስተሳሰብ የሚደረግ ከሆነ ዛሬ ባይሆን ውሎ አድሮ ነገር ይበላሻል፡፡ የዚህ ምሣሌው ይሄውና በኢትዮጵያችን ባልተለመደ ሁኔታ ሁለት ፓትርያርኮች ሊኖሩን ነው፤ ከሁለት ሲኖዶሶች የሚሰፋ አንድ ትልቅ የሲኖዶስ ጀንዲም እንዲሁ፡፡ ምናልባት ጉዳዩን በጥልቀት የሚያውቀው የክርስትናው ዓለም ጥርሱን ተነቅሶ ሊስቅብን ይችላል – ያ እንኳን ግዴለም፤ እንችለዋን፡፡ የይድረስ የይድረስ ነገር እየቆዬ ችግር ማምጣቱን የዘነጋን መስለናል፡፡ “ጨዋ ሲጋባ የተፋታ ያህል ነው” እንደሚባለው ይህ ድርድር ሰዎችን ወይም ቀና አስተሳሰቦችን ላለማስከፋት ከሚል መደላድል ባይነሳና ሁሉ ነገር ተፍረጥርጦ ዕርቁ ቢካሄድ፣ የሢመቱም ነገር የተወነጋገረ ሣይሆን መልክ ያለው ቢሆን መልካም ነበር፡፡ ጭቅጭቅ በፊት ነው፡፡ ንትርክ ሳይስማሙ ነው፡፡ ውል ከተቋጠረ በኋላ ነገር ቢመጣ ሕወሓትንና የዱሮ ኦነግን መሆን ነው – ከዚያም ከፍ ሲል የውጫሌን ስምምነት አንቀጽ 17፡፡ ይሄ ነገር በቅጡ የተሄደበት አልመሰለኝም፡፡

በበኩሌ የሁለት ፓትርያርኮችን መኖር አልደግፍም፡፡ ማንም ይሁን ማን አንድ ፓትርያርክ በቂ ነው ብቻ ሣይሆን በህግ የተደነገገውም ያ ይመስለኛል፤ ጴጥሮስ ላይ ጳውሎስ አልተደረበም፤ ክርስቶስ ላይም ሌላ አልተጫነም፡፡ በተጨማሪም የሲኖዶስ አባላት ብዛት ከወትሮውና ምናልባትም በህግ ከተጠቀሰው በዘለለ ዕጥፍ ሊሆኑ መሰለኝ፡፡ ይህም አይገባኝም፡፡ ስንት እንደነበሩና ስንትም መሆን እንዳለባቸው ባላውቅም ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ከአቅሟ በላይ የሲኖዶስ አባላት ብዛት እንዲኖራት ቢደረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ይመስለኛልና ይሄም ጉዳይ በቅጡ የታሰበበት አይመስለኝም – ለአንዲት ድሃ ሀገር 547 የፓርላማ አባላትን “መርጦ” በሀገሪቱም በሕዝቡም በደናቁርት ዕንቅልፋሞቹም እንደሚቀልደው ሕወሓት ማለት ነው፡፡ ነገረ ሥራው ሁሉ የዚያችን እሽኮለሌ የምትባል ዐይጥና የምጣዱን የትግርኛ ተረት የሚያስታውስ ነው፡፡ “ምዕንቲ ምጎጎ ትህለፍ ዐንጭዋ” ይላሉ እነሐጎስ፡፡  እኔ ደግሞ “አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” እላለሁ፡፡ እናያለን፡፡

ዕርቁ ይደፍርስ እያልኩ አይደለም፡፡ ኦርቶዶክስ ሰላም አትሁን እያልኩ አይደለም፡፡ የኔም ሃይማኖት የሆነችዋ ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ወደ ቀናው መንገድ ብትመጣ በየቀኑ በተኩላ የምትዘረፈውን በሽዎች የሚቆጠር ምዕመን ታድን ነበር፡፡ ችግራችን እንደማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ሁሉ የኛይቱም በሊቀ ሣጥናኤል ቁጥጥር ሥር መግባቷ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ልንናገረው የማንደፍረውን የፈጠጠ እውነት ነው የምናገረው፡፡ በ“ትቀሰፋለህ” ማስጠንቀቂያ የተሸበበ ማኅበረሰብ ውስጥ እውነትን መናገር ሶቅራጠስን መሆን ይጠይቃል፡፡ የዕግሩ ዕጣቢ መሆን የማይቻለኝ እኔ ግን ለአሁኒቷ ቅጽበት ብቻ እሱን ሆንኩ፡፡ “ያበጠው ይፈንዳ!” እንል የለም? አዎ፣ ራሳቸው የኋሊት ቀርተው ሕዝቡንም የኋሊት የሚጎትቱ የአንዳንድ የሃይማኖት አባቶችና ወንድሞች አካሄድ መታወቅና መታረምም አለባቸው፡፡ “በሽታው ያልታወቀ መድሓኒት አይገኝለትም” ይላሉ አበው፡፡

ስላልተነሳሁበት ወደዚህኛው መስመር ባልገባ እመርጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ለብልኅ አባቶችና ወንድሞች ጥቂት ነገር ብተነፍስ ኅሊናየ ጊዜያዊ ዕፎይታ የሚያገኝ ይመስለኛል፡፡ እዚያው ውስጥ ስለነበርኩና ስላለሁም የምለው እውነቴን ነው፡፡

ኦርቶዶክስን ያፈረሳት ሰው አይደለም፡፡ ኦርቶዶክስን ያፈረሳት ደርግ አይደለም – ካቶሊክንና ኢቫንጀሊካን ቤተ ክርስቲያንን ያፈረሷቸው የየሀገራቱ መንግሥታት እንዳልሆኑ ሁሉ፡፡ ኦርቶዶክስን አይሆኑ ሆና እንድትፈረካከስና ክብርና ዝናዋን እንድታጣ ያደረጋት ሕወሓት አይደለም፡፡ ማን ነው ታዲያ ብሎ የሚጠይቅ አይጠፋም፡፡ መልሱ ኦርቶዶክስን ያጠፋት በራሷ ጉያ ያሸመቀው የአጋንንት ኃይል ነው፡፡ ሰይጣን በሰዎች አድሮ ያላጠፋው ቤተ ክርስቲያን የለም፤ የአውሮፓና የአሜሪካ አብያተ ክርስቲያን ወደሙዚየምነትና ወደምሽት ክበቦች እየተለወጡ የሚገኙት በመሢሑ ክርስቶስ ሣይሆን በዲያብሎስ ቀጥተኛ ጣልቃ-ገብነት ነው፡፡ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በስሙ ስንቀልድና ስንዘብት ለክፉ ሥራችን ውጤት አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ምንም እንኳ  እንደመጽሐፉ ሁሉም በኃጢኣት ሥር የወደቀ ቢሆንም ኃጢኣትን እንደዘወትር ልማድ ወስዶ በኃጢኣት መመላለስና የነፍስን መንገድ መሳት ለምን ዓይነት የተንሻፈፈ ሕይወት እንደሚያጋልጥ በግልጽ እያየን ነው፡፡ “ይህ ካህን እንዲህ ሠራ፤ ይህ ፓትርያርክ እንዲህ አደረገ” ማለት አልፈልግም፡፡ ብፈልግ ግን እጅግ ብዙ ነገር መናገር እችላለሁ – ከቅርብ እስከ ሩቅ፡፡ አዎ፣ ዲያቆናትና ካህናት፣ ኤጲስ ቆጶሣት፣ ጳጳሣትና ሊቃነ ጳጳሣት … እናንተ ራሳችሁ ህገ-እግዚአብሔርን በአግባቡ አክብራችሁ በጎቻችሁን ብትመሩ ኖሮ ይህ ሁሉ ውርጅብኝ በሀገራችን ላይ ባልወረደ ነበር፡፡ “ቤታቸውን ከፍተው ሰው ሌባ ይላሉ” የሚል የአራዶች ምሣሌያዊ አባባል አውቃለሁ፡፡ እውነት ነው፡፡  ሰውን ማታለል ቀላል ነው፡፡ ሰማይና ምድርን በሚያንቀጠቅጥ ሽብሸባና ወረብ፣ ቅኔና ማኅሌት፣ ቅዳሤና ዝማሬ መዋሲት… ሕዝበ ክርስቲያንን ማነሁለል ከባድ አይደለም፡፡ ነገር ግን ጸሎትና ምህላውን እግዚአብሔር እንዲቀበለውና በጸሎት የሚጠየቀውን ሳይውል ሳያድር እንዲፈጽም ልባዊ አቀራረብ ያስፈልጋል፤ ከ“እክህደክ ክርስቶስ…” ወጥቶ “እክህደከ ሰይጣን”ን ማጥበቅ ይገባል፡፡ ልብሰ ተክህኖን ማሣመር፣ ጢምን ማንዠርገግ፣ ጥንግ ድርብ ቅብጥርሶ ከካባ ጋር መደረብ፣ የወርቅና የአልማዝ መስቀሎችን ደረት ላይ መኮልኮል፣ ዜማና አቋቋምን፣ ድጓና ፆመ ድጓን ሸምድዶ ሲያነበንቡ ማደርና መዋል፣ በመረዋ ድምፅ ቅዳሤንና ማኅሌትን ማመልጠን…. ብቻውን የትም እንደማያደርስ ባለፉት 40 እና 50 ዓመታት በሚገባ ተገንዝበናል – እውነት ብትቆጠቁጥም ልንክዳት ግን አይገባም፡፡ ከነተረቱ “ሣል ይዞ ስርቆት፣ ቂም ይዞ ጸሎት” እንላለን፡፡ የኛ ግን ከተራ ቂምና ጥላቻም ባለፈ አሠርቱ ትዕዛዛትን ሙሉ በሙሉ ካልጣስን እግዚአብሔር ጸሎታችንን ቅቡል አያደርገውም የተባልን ይመስል ከፖለቲከኞቹ በበለጠ በሰይጣናዊ የጭለማው መንግሥት ተውጠን ስንዳክር እንገኛለን – ከሞላ ጎደል ሁላችንም፡፡ በዚያ ላይ ዘረኞች ነን፡፡ ጎጠኞች ነን፡፡ እግዚአብሔርን የማናውቅ ሞልተናል፡፡ የምንሰብከውን የእግዚአብሔር ቃል እንደበቀቀን  እየደጋገምን ከመናገር ባለፈ የእውነቱን ሕይወት አንኖረውም፤ እንደቀደምቱ ጻፎችና ፈሪሣውያን አስመሳዮች እንበዛለን፡፡ ሕዝቡ ታዲያ ማንን ዐይቶ ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ? በቆሻሻ ቱቦ የሚያልፍ ፈጣሪ ቀርቶ ሰውም የለም፡፡

ኤዲያ ባልተነሳሁበት ጉዳይ ገብቼ ዘባረቅሁ፡፡ ይቅርታ፡፡ መፍትሔው ግን – እደግመዋለሁ -መፍትሔው  የምንለውን ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ይቺ “የምናደርገውን ሳይሆን የምንለውን ስሙ” የምትባል ማጭበርበሪያ ደግሞ ነፍሶባታልና ትቅር፤ ወጣቶችም ጎልማሦችም የ“ባነኑባት” መሰለኝ፡፡ ይልቁንስ “አንተ ያልቻልከውን ምሥጢር ለኔ አትንገረኝ” ብሎ ለጓደኛው የተናገረውን ሰው ጀግንነት እንቀበልና የማናደርገውን አንናገር፤ የምንናገረውን ደግሞ በድርጊት እናሳይ፡፡ ህገ እግዚአብሔርን እናክብር፡፡ ቤተ ክርስቲያንን አንናቅ፤ የእግዚአብሔርና የሰው የጊዜ አቆጠጣር በመለያየቱ ምክንያት ተስፋ እየቆረጥን ከምናደርጋቸው አልባሌ ነገሮችም እንቆጠብ – እርሱ የማያየው ነገር አንድም የለም፡፡ ዛሬ ስላልቀሰፈን የተወን ወይም ሥራውን የረሳ እንዳይመስለን፡፡ አንዳንዴ ሳስበው እግዚአብሔር መኖሩን ጭምር የሚክዱ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እንደሚኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ እንደሀገርም እንደሕዝብም የገባንበት አዘቅት ልኬት የለውም፡፡

የንስሃን እውነተኛ ትርጉም ደግሞ እንወቅ፤ ንስሃ ማለት ለታጥቦ ጭቃነት ዋስትና እንዳልሆነም እንረዳ፡፡ በስመ “እግዚአብሔር መሓሪ ነው” ያሻንን ወንጀልና ኃጢኣት ብንሠራ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ የልባችንን ተንኮል ያውቃልና ይፈርድብናል፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ይልቁንስ ሰዎች ከሰዎች ከሚያደርጉት ዕርቅ ይልቅ – እሱም ውብ መሆኑ እንዳለ መሆኑ ተይዞልኝ –  በቅድሚያ እኛ ኢትዮጵያውያን ከፈጣሪያችን ጋር ዕርቅና ሰላም ብንፈጥር የተሻለ ነው፡፡ ከእርሱ መራቃችን ነው ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ችግር የዳረገን ብዬ አምናለሁ፡፡ እንጂ ከሦስትና አራት ሚሊዮን ሕዝብ የወጡ እፍኝ የማይሞሉ ሽፍቶች ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት 90 እና 100 ሚሊዮን ሕዝብ እንዲህ እያንቀጠቀጡ ባልገዙ ነበር፡፡ እናም ችግሮቹም መፍትሔዎቹም እኛው ነን፡፡  “ምንትስ ያላሉበት እንትን አያፍሩበትም” ቢባልም በዚህች መጣጥፍ ያስቀየምኳችሁ ሰዎች መኖራችሁ አይቀርምና ዘመኑ የይቅርታና ምሕረት እንደመሆኑ ሳይውል ሳያድር ዛሬውኑ በትኩሱ ይቅር በሉኝ – የሀገር ጉዳይ ሆኖብኝ እንጂ ወድጄ አይደለም፡፡ እኔም የእግዚአብሔር ምሕረት በእጅጉ የሚያስፈልገኝ በዳይና ኃጢኣተኛ መሆኔን አውቃለሁ፤ “በሌሎች ዐይን ውስጥ ያለችውን ነቁጥ የምታህል ስንጥር ቆሻሻ ለማውጣት ከመሞከርህ በፊት በራስህ ዐይኖች ውስጥ የተጋደመውን ዕርፍ እሚያህል ጉድፍ ቀድመህ አውጣ” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሣዊ አስተምህሮም እንዳልዘነጋሁ በዚህ አጋጣሚ ማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡  ….  ([email protected])

Leave a Reply