‘አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ ታገደ፤ የወንጀል ምርመራም ሊጀመርበት ነው

‘አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ2 ሚልየን ብር በላይ የተደረገለት የበጀት ድጋፍ በአመራሮቹና አባላቱ በመመዝበሩ ታገደ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፓርቲው ሂሳብ ላይ የተደረገ የኦዲት ምርመራን በተመለከተ የተገኘውን ውጤትና ውሳኔ የያዘ ባለሥምንት ገጽ መግለጫ ዛሬ መጋቢት 4 ቀን 2016 ይፋ አድርጓል።

ቦርዱ በ2015 ዓመት 2 ሚልየን 750 ሺህ 873 ብር ለ’አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ ገቢ አድርጎ የነበረ ሲሆን የፓርቲው አባል በዚህ ዓመት በጥቅምት ወር ባስገቡት ጥቆማ መሰረት ገንዘቡ ለፓርቲ እንዳልዋለ እና “በሊቀ መንበሩ ለግል ጥቅም እየዋለ” በመሆኑ እንዲጣራ ተደርጓል።

በህዳር 2016 ለፌደራል ዋና ኦዲተር የፓርቲው ሂሳብ እንዲመረመር የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳወቀ ሲሆን የበጀት አጠቃቀምን በተመለከተ የግልጽነትና ተጠያቂነት አሰራር ፓርቲው አለመዘርጋቱ በምርመራው ታውቋል።

ፓርቲው ከቦርዱ ከተሰጠው ገንዘብ ከ2 ነጥብ 5 ሚልየን ብር በላይ የሚሆነውን የተጠቀመ ቢሆንም በተቋሙ የወጪ አርዕስት/ዝርዝር ላይ በአግባቡ አለመመዝገብ፣ ዕውቅና ያላገኙና ያልጸደቁ ወጪዎች፣ በቃለ ጉባዔ ያልጸደቁ ተመላሽ ብድር ተብለው ለአባላት የተሰጠ ገንዘብ፣ ለባንክ የተጻፈ ደብዳቤ በሌለበት ከአንድ ሚልየን ብር በላይ ለአበል ወጪ በማድረግ ፓርቲው የኦዲት ክፍተት ተገኝቶበታል።

የኦዲት ምርመራውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ‘አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ የተደረገለትን የገንዘብ ድጋፍ “ለታለመለት ዓላማ እንዳላዋለ እና ከፍተኛ ገንዘብ በፓርቲው አመራሮችና ለሌሎች አባላት የግል ጥቅም እንዲውል መደረጉን” ተገንዝብያለሁ ብሏል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ የካቲት 28 ቀን 2016 ባካሄደው ስብሰባ በኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት ፓርቲው እና አመራሮቹ የተፈጸመው ወንጀል እስከሚጣራ ድረስ እንዲታገዱ ወስኗል።

በተጨማሪም የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር እንዲሁም የተመዘበረውን ገንዘብ በተመለከተ የፍትሐ ብሔር ክስ እንዲመሰረትና ገንዘቡ ለቦርዱ ተመላሽ እንዲደረግ ውሳኔ ማስተላለፉን አዲስ ማለዳ ከቦርዱ መግለጫ ተመልታክለች።

Source: Link to the Post

Leave a Reply