አንጋፋው ጋዜጠኛ እና አርበኛ ደምስ በለጠ የሀገር ባለውለታ በመሆናቸው በትውልዱ ዘንድ ሊዘከሩ እንደሚገባ ቤተሰቦቹ ተናገሩ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አማሚ ታህሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም…

አንጋፋው ጋዜጠኛ እና አርበኛ ደምስ በለጠ የሀገር ባለውለታ በመሆናቸው በትውልዱ ዘንድ ሊዘከሩ እንደሚገባ ቤተሰቦቹ ተናገሩ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አማሚ ታህሳስ 12 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የአማራ ሚዲያ ማዕከል የአንጋፋው ጋዜጠኛ እና አርበኛ ደምስ በለጠን ሁለተኛ ዓመት ሕልፈትን በማሰብ አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የቤተሰቦቹ ቤት አቅንቷል። በእለቱም የጋዜጠኛ ደምስ በለጠን እናት ወ/ሮ አሳመነች ይማምን ያነጋገረ ሲሆን ወ/ሮ አሳመነችም ትውልዱ ሁለገብ የሆኑ ጀግና ልጃቸውን እንዲዘክርና ከመልካም አበርክቷቸውም ትምህርትን እንዲቀስም መክረዋል። ጋዜጠኛ ደምስ ከጋዜጠኝነት ባሻገር በአርበኝነቱም ኤርትራ በርሃ ድረስ በማቅናት ታጋዮችን በማነቃቃትና በመደገፍ የነበራቸው አስተዋፅኦ መረሳት እንደሌለበት ተጠቁሟል። የጋዜጠኛ ደምስ እህት ወ/ሮ አዜብ በለጠ በበኩሏ ወንድማችን የተገደለው ሁላችንም በሚያም መልኩ ከምግብ ምረዛ ጋር በተያያዘ በክፉዎች ሴራ መሆኑን ገልጻለች። ጋዜጠኛው አምባገነኑን ስርዓት በመቃወም በኩል የአላማ ፅናት ስለነበረው ወደ ሀገሩ እንኳ እንዳይገባ ብዙ ፈተናዎች ይገጥሙት እንደነበር ገልጻ ከ32 ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ወደሚወዳት አገሩ ኢትዮጵያ ከተመለሰ 3 ሳምንት ሳይሆነው በእኩዮች ሸፍጥ መገደሉን አውስታለች። ደምስ በለጠ ለውጥ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ባለውለታ ስለመሆኑ የጠቆመችው ወ/ሮ አዜብ አሁን ላይ ላለው የወያኔ መንኮታኮት በብዕራቸውና በመድረክ ፊት ለፊት ያለምንም ፍርሃት ለበርካታ ዓመታት የታገሉት የእነ ደምስ ሚና ከፍተኛ ነበር ብላለች። የደምስን ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያንም በቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን በነገው እለት ተገኝተው በሻማ ማብራትና በፀሎተ ፍትሃት እንደሚዘከሩምወ/ሮ አዜብ አስታውቃለች። አንጋፋው ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ከ32 ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ህዳር 23 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ የመጡ ሲሆን ታህሳስ 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጉዳዩ የበለጠ የሚጣራ ሆኖ ባጋጠማቸው የምግብ ምረዛ በተወለዱ በ56 ዓመታቸው ህይወታቸው ማለፉ ይታወቃል። ከጋዜጠኛ እና አርበኛ ደምስ በለጠ ቤተሰቦች ጋር ያደረግነውን ቆይታ በአሚማ የዩቱብ አድራሻ የምናጋራ ይሆናል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply